የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

114

ሐረር ፣ ኅዳር 20 ቀን 2014(ኢዜአ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 6 ሚሊየን ብር የሚገመቱ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጤና መምሪያ አደረገ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ ድጋፉን ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሐመድ አስረክበዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ድጋፉ በጤና ተቋማት የሚታየውን የህክምና መገልገያዎች እጥረት ለማቃለልና ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ እያካሄደ ላለው የጥናትና ምርምር ሥራ እገዛ ያደርጋሉ።

በተለይ ዩኒቨርሲቲው የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የጀመረውን “ቻምፕስ” የተሰኘ ፕሮጀክት ለማሳካት አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም አስታውቀዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ በበኩላቸው “የህክምና ቁሳቁሶቹ ድጋፍ በዞኑ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል የሚያስችል ነው” ብለዋል።

በዚህም በጤና ጣቢያ ደረጃ ለእናቶችና ህጻናት እየተሰጠ ላለው የጤና አገልግሎት ውጤታማነት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለዋል።

የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሃመዲን ከቢር ሁሴን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ያደረገው የሕክምና መገልገያዎች ድጋፍ በአንድ ሆስፒታልና 13 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እንደሚውሉ አስታውቀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በድጋፍ ካበረከታቸው የሕክምና መገልገያዎች መካከል አልትራ ሳውንድ መመርመሪያ መሣሪያዎች፣የህሙማን አልጋዎች፣ ዊልቸሮች፣ የደም መጠን መመርመሪያዎች  ይገኙባቸዋል።