የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነትን ለማስከበር አንድነታችንን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

131

ሐረር፣ ኅዳር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነትን ለማስከበር አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ሲሉ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሱልጣን አብዱሰላም አሳሰቡ።

በዓለም ለ24ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ12ኛ ጊዜ የመቻቻልና የአብሮነት ቀን ዛሬ በሐረር ከተማ ተከብሯል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ”የመቻቻል የመከባበር ከተማ” ተብላ የተሰየመችው ሐረር በዓሉን ለአንድ ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበር ጀምራለች።  

አፈ ጉባዔ ሱልጣን በበዓሉ የመክፈቻ ሥነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያን ለመበታተን ከውጭም ከውስጥ የተነሱትን ጠላቶችን አፍራሽ ተልዕኮ ለማምከን አንድነታችንን ማጠናከር  ይገባናል ብለዋል።

በአሸባሪውን ህወሓት የተጋረጠውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ በአጠረ ጊዜ ለመቀልበስ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ትግል ስኬት  የክልሉ ሕዝብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሕልውና ትግሉን በግንባር በመምራት ያሳዩት ኢትዮጵያዊ የጀግንነት ተጋድሎ ለሁሉም አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ጠቅሰው  አድናቆታቸውን ቸረዋል።

የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በስንቅ ፣ በገንዘብ፣ በደም በመለገስ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አፈ ጉባዔው አሳስበዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ያገጠመውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ በግንባር በመፋለም ላይ ላሉ የፀጥታ ኃይሎች ቤተሰቦችን በመደገፍ የመቻቻልና የአብሮነት ባህላችንን ማሳየት ይገባልም ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልጀባር መሐመድ በበኩላቸው የክልሉ ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሀገርን ለማዳን በግንባር ለሚገኙ የፀጥታ አካላትና የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም  ጠይቀዋል፡፡