የኢኮኖሚ ጫናውን ለመቋቋም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል

48

ህዳር 20/2014 (ኢዜአ) የአገር ውስጥ አምራቾች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እና ጥራትን በማረጋገጥ የኢኮኖሚ ጫናውን መቋቋም እንደሚገባ በኢንደስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለኃብቶች ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለሃብቶች እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አሜሪካ ለታዳጊ አገራት ከምትሰጠው ከቀረጥ ነጻ የንግድ ዕድል /አጎዋ/ በመውጣቷ የምታጣውን ገቢ ለመተካት የገበያ ተደራሽነትን ማስፋት ይገባል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የአምራች ኢንደስትሪ ዘርፍ አካላት የፋብሪካ ውጤቶቻቸውን በጥራትና በብዛት በማምረት የኢኮኖሚ ጫናውን መቋቋም እንደሚቻል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንደስትሪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ጌታቸው ኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መንገዶች ኢኮኖሚያዊ ጫና እየደረሰባት መሆኑን ጠቁመዋል።

እነዚህን የውጭ ጫናዎች ለመከላከል ምርቶቻችንን በጥራትና በብዛት በማምረትና ከአሜሪካ ውጭ ለሆኑ የውጭ አገራት ገበያዎች በስፋት ማቅረብ ይገባል ብለዋል።

በተለይ ብዙ ያልተሰራበትን የአፍሪካን ገበያ መጠቀም እንደሚገባ በመጠቆም።

በተጓዳኝም ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ አገሪቷ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት እንደሚገባ ጠቁመው በቆዳና ቆዳ ውጤቶች የታዩ ለውጦች በሌሎችም ዘርፎች መደገም አለባቸው ብለዋል።

በቆዳ ኢንደስትሪ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ዘላለም መራዊ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያላትን ጥሬ ኃብት በአግባቡ በመጠቀም በተለይም በእስያና በአፍሪካ ያለውን የገበያ ዕድል መጠቀም አለባት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከአጎዋ በዓመት የምታገኘው ገቢ ከ250 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም ያሉት ባለኃብቱ ይህንን ገቢ በአፍሪካና በእስያ አገራት ገበያ ማካካስ እንደምትችል ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲሴ ጋርከቦ፤ በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ ኢኮኖሚ እንዳይጎዳ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ የተቀናጀ አሰራር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ከውጭ የሚገቡ የምግብ ውጤቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ያስፈልጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን የምግብ ዘይት በግማሽ መጠን በአገር ውስጥ እንዲመረት በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑንም ለአብነት ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ ምርቶች በጥራትና በብዛት ለገበያ ከቀረቡ እንደ አጎዋ ያሉ በአገር ሉዓላዊነት ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ አሰራሮችን መቋቋም እንደሚቻልም አስረድተዋል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዕቅድ ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ሕሉፍ በበኩላቸው የአገሪቷ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን በጥራት የሚያቀርቡ ከሆነ በአውሮፓና እስያ ሰፊ የገበያ ዕድል መኖሩን ተናግረዋል።

በመሆኑም የአምራች ኢንደስትሪ ባለሃብቶች በዚህ ላይ ትኩረት በማድረግ አገሪቷ ላይ ሊመጣ የሚችለውን የኢኮኖሚ ጫና ከወዲሁ መቋቋምና ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚቻል አሳስበዋል።

ባለኃብቶቹ ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ በድል እስከምትሻገር ባለሃብቱ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው ለዚህም ቁርጠኛነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም