በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተዋቀረው የሚኒስቴሮች ግብረ-ሀይል ስራ ጀመረ

ህዳር 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተዋቀረው የሚኒስቴሮች ግብረ-ሀይል ዛሬ በይፋ ስራ መጀመሩን አስታወቀ።

ግብረ-ሀይሉ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግሰታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት በጋራ በተደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ላይ የተመላከቱ ምክረ-ሀሳቦችን ተግባራዊ ያደርጋል።

ለዚህም በግጭቱ ምክንያት የተፈጸሙ ሁሉንም ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚሸፍን የተጠቃለለ ስትራቴጂና የድርጊት መርሀ-ግብር ማጽደቁን ጠቁሟል።

መንግስት ከወሰደው የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም እርምጃ በኋላ በአፋር እና አማራ ክልል ተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚመለከትም በመግለጫው አትቷል።

ግብረ-ሀይሉ ስራውን በውጤታማነት ለማከናወን እንዲያስችለው አራት ኮሚቴዎችን ማዋቀሩን ገልጿል።

የወንጀል ምርመራ እና ክስ ኮሚቴ በፍትህ ሚኒስቴር፣ የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ጉዳዮች ኮሚቴ በሰላም ሚኒስቴር፣ የጾታዊ ጥቃቶች ኮሚቴ በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዲሁም የሀብት ማሰባሰብ ኮሚቴ በገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚመሩ አመላክቷል።

የግብረ-ሀይሉን እና የተዋቀሩትን ኮሚቴዎች የቀን ተቀን ስራዎች ለማስተባበር፣ ለመከታተል እና ለማቀናጀት ይቻል ዘንድ ጽ/ቤት እንዲቋቋም መወሰኑንም መግለጫው ጠቅሷል።

ግብረ-ሀይሉ ለወንጀል ምርመራ እና ክስ ኮሚቴ የተፈጸሙ ጥሰቶችን አስመልከቶ ጠንካራ እና ግልጽነት ያለው የህግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ እንዲቻል አስፈላጊው የሞያ ነጻነት ያለው ልዩ የወታደራዊ እና መደበኛ ጥምር የወንጀል ምርመራ እና ክስ የስራ ክፍል በማቋቋም ስራ እንዲያስጀምር አቅጣጫ አስቀምጧል።

ኮሚቴዎች ተጎጂን ማዕከል ያደረገ የአሰራር ስርዓትን እንዲከተሉ እና ትኩረታቸውም ተጎጂዎች እውነትን የማወቅ እና ፍትህ የማግኘት መብቶቻቸው እንዲከበሩ እንዲሁም አቅም በፈቀደ መጠን የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እና ካሳ የሚያገኙበትን ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንዲያተኩሩ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በተጨማሪ የፍትህ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብረ-ሀይሉ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ይችል ዘንድ አግባብነት ካላቸው ሀገራዊ እና አለምአቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከአቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ የቴክኒክ እርዳታ እና ድጋፍ እንዲገኝ ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የስራ መመሪያ መስጠቱን መግለጫው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም