እንዳሻው አላዩ በዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር የሁለተኛ ዙር ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል

78
አዲስ አበባ ነሀሴ 17/2010 በሃንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት እየተካሄደ ባለው 6ኛው የዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የሚወዳደረው እንዳሻው አላዩ  ሁለተኛ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል። የቦክስ ውድድሩ ከትናንት በስቲያ መጀመሩ ይታወቃል። ከትናንት በስቲያ በ49 ኪሎ ግራም የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው እንዳሻው አላዩ ኢኳዶራዊውን ቦክሰኛ ጆናታን ሜርቻንን በነጥብ በማሸነፍ ወደ 16 ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ነው። እንዳሻው የሁለተኛ ዙር ጨዋታውን ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ከአርሜንያዊው ሴይራን ዬጊክያን ጋር እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። እንዳኛው የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ወደ ስምንት ውስጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል። ትናንት በ48 ኪሎ ግራም ኢትዮጵያን ወክላ የተጫወተችው ሀና ደረጀ በአሜሪካዊቷ ሳንድራ ቶቫር ተሸንፋ ከውድድሩ ውጭ መሆኗን ተናግረዋል። በሃንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት የሚካሄደው 6ኛው በዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም