በጦር ግንባር ከሚደረገው ውጊያ ባሻገር ሁላችንም በተሰማራንበት ውጤታማ በመሆን ለአገራችን መስራት

137

ህዳር 19/2014(ኢዜአ) አሸባሪዎችን ለመፋለም በጦር ግንባር ከሚደረገው ውጊያ ባሻገር ሁላችንም በተሰማራንበት ውጤታማ በመሆን ለአገራችን መስራት አለብን ሲል አርቲስት ደሳለኝ ሃይሉ ተናገረ።
የኪነ-ጥበብና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሀገራቸው ላይ የተከፈተውን ሁለንተናዊ ጦርነት በጥበብ ስራዎቻቸውና በእለት ተእለት ተግባራቸው በመመከት በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋልም ነው ያለው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ግንባር መዝመታቸው የቀደሙ ታላላቅ የኢትዮጵያ መሪዎችን ፈለግ የተከተሉበት ተግባር መሆኑንም ጠቅሷል።

አሸባሪዎችን ለመፋለም በጦር ግንባር ከሚደረገው ውጊያ ባሻገር ሁሉም በተሰማራበት አሸናፊና ውጤታማ በመሆን የዜግነት ግዴታውን መወጣት አለበትም ነው ያለው።

”ኢትዮጵያዊያን በነፃነትና በክብራቸው የማይደራደሩ፤ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከኩ በመሆናቸው አሁንም በእጅ አዙር በምዕራባውያን ፊታውራሪነት እየተደረገ ያለውን ጦርነት ያለጥርጥር ያሸንፋሉ” ነው ያለው።

በመሆኑም የሕልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ በሐገር ውስጥ ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በመላው አለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉ ያለውን የገንዘብና ሌሎች ድጋፎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል።

ሁላችንም ሰራዊቱን ከመደገፍና ከማገዝ በተጨማሪ የተፈናቀሉ ወገኖችንም ልንደርስላቸው ይገባል ብሏል።

አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ቆምንለት ከሚሉት አላማ በተቃራኒ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቁሞ በተለይም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና የኪነ ጥበብ ሰዎች እውነታውን ለዓለም በማሳየት ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ብሏል።

”ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በነገሮች ተፈትና በፅናት አልፋቸዋለች፤ አሁንም በትብብርና በመተጋገዝ እናልፋቸዋለን” ብሏል።