ሁላችንም በያለንበት አካባቢ ሰላምና ጸጥታችንን እየጠበቅን ነው

105

ህዳር 19/2014(ኢዜአ) ሁላችንም በያለንበት አካባቢ ሰላምና ጸጥታችንን እየጠበቅን ነው፤ የኢትዮጵያን ጠላቶች በጋራ ለመመከት ተዘጋጅተናል ሲሉ የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በአዲስ አበባ የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት ነዋሪዎች ሁላችንም በያለንበት አካባቢ ሰላምና ጸጥታችንን እየጠበቅን ነው፤ የኢትዮጵያን ጠላቶች በጋራ ለመመከት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የክፍለ ከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ሀሊማ ረሂማ በአካባቢያቸው የተለያዩ ድጋፎችን በማሰባሰብ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ የሚያደርጉትን እገዛ  አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ከድጋፉ ባሻገር አካባቢያቸውን ከሰርጎ ገቦች በመጠበቅ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ በመናገር ሀብረተሰቡ በተሰማራበት የሙያ መስክ ጠንክሮ በመስራት ደጀንነቱን ማሳየት አለበት ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ስንቄ በቀለችም ለአካባቢያቸው ብሎም ለከተማቸው ሰላም እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ የተቻላቸውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ  ኦሜጋ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ለመከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለው ድጋፍና የሞራል እገዛ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አሸባሪው የሚያደርገው ጥረት በተባበረ ክንዳችን እየከሰመ ነው፤ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት እናስጠብቃለንም ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተለያዩ የወጣትና ሴቶች አደረጃጀቶች የተሳተፉ ሲሆን ለመከላከያ ሰራዊት የስንቅ ዝግጅት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም