የሀገራችንን ከብርና ነፃነት ማስቀጠል ተራው የኛ ነው

121

ሀዋሳ ፤ ህዳር 19/2014(ኢዜአ) የሀገራችንን ክብርና ነፃነት ለማስቀጠል የምንችለውን ሁሉ የማድረግ ተራው የኛ ነው ሲሉ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፍሰር ፀጋዬ ቱኬ ተናገሩ፡፡
በከተማዋ  ከሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና አሸባሪው ላፈናቃላቸው ወገኖች   የሚውል ከ70 ነጥብ 8ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጥሬ ገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ድጋፉን በተረከበበት ወቅት ከንቲባው እንዳሉት፤ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ምዕራፍ ለሀገር ሠላምና ሉአላዊነት ሁሉም የበኩሉን ማድረግ የሚጠይቅበት ጊዜ ነው።

ለመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ምልክትና የፓን አፍሪካ ንቅናቄ ፋና ወጊ የሆነችው ኢትዮጵያ ለነጭ ቅኝ ገዢዎች ሳትንበረከክ እንድትቆይ ጀግኖች አባቶች መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰው፤ የሀገራችንን ክብርና ነፃነት ለማስቀጠል የምንችለውን ሁሉ የማድረግ ተራው የኛ ነው ብለዋል፡፡

ነፃ የሆነች ሀገር ተረክበን ማስቀጠል ካልቻልን ነገ የታሪክ ተወቃሾች እንሆናለን ያሉት ከንቲባው፤ ኢትዮጵያዊ ወይም ኢትዮጵያ መሆን የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መርህ በመከተል ሁሉም ሰው ለሀገሩ ጥሪ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍ የመጀመሪያው ምዕራፍ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ከ70 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን ሊያዋርዷት የቋመጡ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿን እስክታሳፍር ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሚልኪስ አኔቦ፤ የምዕራባውያንን አጀንዳ ለማሳካት የሚሰራው አሸባሪው ህወሃትና ተላላኪዎቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ብዙ ቢሰሩም ሁላችንም በመተባበራችን እያሸነፍን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በዱር እያደረ ለሀገሩ ክብር መስዋዕትነትን እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነጋዴው ማህበረሰብ የተሰበሰበው ድጋፍ ቀጣይ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዙር ከከተማው የንግድ ማህበረሰብ ከ10 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ደግሞ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መደረጉን አመላክተዋል፡፡

የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ገለታ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን ለመታደግ የቀረበውን የክተት ጥሪ ተከትሎ የሶስተኛ ዓመት የጤና መኮንንነት ተማሪ ልጃቸውን ወደ ግንባር መርቀው መሸኘታቸውን ተናግረዋል።

ሁሉ ነገር የሚያምረው ሀገር ስትኖር እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ሙሉ፤ ደጀን ከመሆን ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደዘመቱት ሁሉ እኛም ወደ ግንባር ዘምተን ሀገራችንን ለመታደግ ዝግጁ ነን ብለዋል ፡፡

ሌሎች በግንባር ከጠላት ጋር ሲፋለሙ እኛ ደግሞ የከተማችንን ሠላም ለማስጠበቅ ከቀበሌ አመራር አካላት ጋር በመቀናጀት በምሽት የሮንድ ጥበቃ እያደረግን ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

ዛሬ ከተደረገው ጠቅላላ ድጋፍ 60 ሚሊዮን የሚጠጋው በጥሬ ገንዘብ፤ ቀሪው ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተው ደግሞ አልባሳት፣ የምግብ ዱቄት፣ በሶ፣ ዘይትና ሌሎች ቁሶችን ያካተተ መሆኑ ተመልክቷል።

ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና አሸባሪው ላፈናቀላቸው ወገኖች እንዲውል የተደረገው ድጋፍ በሀዋሳ ከተማ ከሚኖሩ ነጋዴዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች  የተሰበሰበ ነው።