በ"ኢትዮጵያ ትጣራለች " የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር 160 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በ"ኢትዮጵያ ትጣራለች " የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር 160 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ

ህዳር19/2014(ኢዜአ) በጎንደር ከተማ አስተዳደር አስተባባሪነት ‘ኢትዮጵያ ትጣራለች’ በሚል በአዲስ አበባ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ 160 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ፡፡
የተሰበሰበው ገቢ በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው ሰራዊት እና ለተፈናቃይ ወገኖች መሆኑን ተጠቁሟል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ፤ የጎንደር ህዝብ አከባቢውን በንቃት በመጠበቅ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ህዝቡ አከባቢውን ከመጠበቅ ጎን ለጎንም ለአገር ህልውና እተዋደቀ ለሚገኘው የጸጥታ ሃይል ደጀን በመሆን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ህዝቡ እስከአሁን ባደረገው ድጋፍም ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ መታደግ መቻሉን ገልጸው አሁንም የህልውና ድጋፉ በድል እስኪጠናቀቅ ድጋፉ አንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በዛሬው ዕለትም በጎንደር ከተማ አስተባባሪነት በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው ሰራዊት እና ለተፈናቃይ ወገኖች በአዲስ አበባ ገቢ መሰባሰቡን ገልጸዋል፡፡
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩም 160 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ጠቁመው ይህን ላደረጉ ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ምስጋናቸውን አቅረበዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኘው አርቲስት ታማኝ በየነ፤ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ሁሉም ሰው የበኩሉን ማድረግ አለበት ብሏል፡፡
ሁሉችንም በአንድ ልብ ከተነጋገርን ይሄን የመከራ ጊዜ እናልፈዋለን ያለው አርቲስቱ ይህ ከሆነም የኢትዮጵያ ሰላም የሚረጋገጥበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆንም ተናግሯል።
በዚህ ጊዜ ሁሉም ከኢትጵያ ጎን መቆም እንዳለበት በመጠቆም ይህ ካልሆነ ግን በታሪከ እና ህሊናው ይጠይቀዋል ሲል ተናግሯል።
የጎንድር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክትር አስራት አጸደወይን፤ "በኢትዮጵያ ትጣራለች " መርሃ ግብር ዩኒቨርሲቲው 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሁለት ጊዜ ደመወዙን መለገሱን ገልጸው ለተፈናቃይ ወገኖችም አልባሳት እና ምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 5 ሚሊዮን ብር፣ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ 2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ብር፣ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ 3 ሚሊዮን ብር፣ ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ 1 ሚሊዮን ብር፣ ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር፣ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ 1 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ገብተዋል።
በተጨማሪም ባለሃብቱ ወርቁ አይተነው 50 ሚሊየን ብር ፣ ጎመጁ ኦይል ኢትዮ ጵያ 20 ሚሊየን ብር፣ በርካታ ግለሰቦች፣ ተቋማት እና ድርጅቶችም ለመለገስ ቃል ገብተዋል።