ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ተከትለን በግንባርና በደጀን የሀገራችንን ህልውና ለማረጋገጥ እንታገላለን

79

ድሬዳዋ፤ ህዳር 19/2014(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን በመከተል በግንባርና በደጀን የሀገራችንን ህልውና ለማረጋገጥ እንታጋላለን ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ።
የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮችና አባላት በድርጅቱ የሩብ በጀት ዓመት  የሥራ አፈጻጸም ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ ላይ  የአስተዳደሩ የፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት፤ አሜሪካ ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ከአሸባሪው ህውሃት ጋር በመተባበር ደካማና የተበታተነች ሀገር ለመፍጠር የሚያካሄዱት ሴራ በተባበረ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ክንድ ይሰበራል፡፡

ይህንኑ እውን እያደረጉ የሚገኙት ጀግናው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን በመከተል በግንባርና በደጀን አስፈላጊውን መስዋዕትነት በመክፈል የሀገር ህልውና እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡

"አባቶቻችንን በታላቅ ፍቅር ፣በመተባበርና አንድነት በአድዋ ላይ ያስመዘገቡትን ድል እኛም የአሁኖቹ ትውልዶች የተደቀነብንን ሴራ በማክሸፍ የበለፀገችና የታፈረች ኢትዮጵያን ለልጆቻን እናወርሳለን ብለዋል ሰብሳቢው፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ አስተዳደር  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፤ የሀገርን ህልውና ለማረጋገጥ እየተካሄደ የሚገኘውን የህልውና ጦርነት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ከአመራሩና እስከ አባላት ድረስ በግንባርና በደጀን አስፈላጊውን ሁሉ እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

እነዚህን ጅምሮች ከማጠናከሩ በተጓዳኝ  ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ የማጠናከር፣ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የፓርቲው አመራሮችና አባላት በየትኛውም የሀገራችን የህልውና ማረጋገጥ ዘመቻ ግንባር ቀደም በመሆን በሁሉም መስክ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት መወጣታቸውን እንዲያጠናክሩም አሳስበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተሣተፉት ሌሎች አመራሮችና አባላትም  የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመከተል የህልውና ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ  በግንባርና በደጀንነት ተሰልፈው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በተለይ  በምጣኔ ሃብት፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር መረጋገጥ፣ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ ፣ የሽብርተኞቹን ህውሃትና ሸኔ ተላላኪዎች ለህግ በማቅረብ ፣ለሠራዊቱ ስንቅና ሃብት በማሰባሰብ በኩል ውጤታማ ሥራ ለማከናወን በቁርጠኝነት እየተጉ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም