ሀሰተኛ መረጃ ሊፈጥር የሚችለውን ቀውስ ለመግታት ፈጣን፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ማድረስ ይገባል

196

ህዳር 19/2014 (ኢዜአ) ሀሰተኛ መረጃ ሊፈጥር የሚችለውን ቀውስና አለመረጋጋት ለመግታት ፈጣን፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የሚደርስበትን የአሰራር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቆመ።
አራተኛው የመረጃ ነጻነት ቀን በአዳማ ከተማ የተከበረ ሲሆን በእለቱ የመረጃ አስፈላጊነት የዜጎች መብትና ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል።

የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ምሁሩ ዶክተር ጌታቸው ድንቁ፤ በቀውስ ወቅት የመረጃ አሰጣጥን ሁኔታ የሚዳስስ የውይይት መነሻ ጸሁፍ አቅርበዋል።      

ዶክተር ጌታቸው በፅሁፋቸው በአንድ አገር ላይ ቀውስ ወይም አደጋ ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቁመው በዚህ ወቅት ተክክለኛና ፈጣን መረጃ ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።  

በተለይም ባደጉት አገራት የተፈጥሮ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት ለዜጎቻቸው የተሟላ መረጃ በመስጠት ራሳቸውን ከአደጋው እንዲያርቁና እንዲጠነቀቁ ያደርጋሉ ብለዋል።  

በኢትዮጵያም እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ለዜጎች ፈጣን፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የሚደርስበት ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት ዶክተር ጌታቸው።   

የሚመለከታቸው አካላት የህዝብ ግንኙነት ሰዎችና ኃላፊዎች መረጃዎቸን በአግባቡ አደራጅተው ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።    

መረጃ ዜጎች ደረጃው ከፍ ያለ ህይወት እንዲመሩ ከማገዙም በላይ ለሰለጠነ ፖለቲካ መጎልበት ያለው ድርሻም የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።    

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ዶክተር መሰንበት አሰፋ፤ ሀሰተኛ መረጃ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለመመከት ትክክለኛ መረጃዎች ተደራሽ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።  

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲኖርም አዋጁ ላይ ያሉ መመሪያዎች፣ ህጉ ምን ይላል የሚለውን በአግባቡ ማስገንዘብ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የመረጃ ፍሰቱ ወደ ዲጂታል እያመዘነ በመሆኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ማሳደግ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባልም ነው ያሉት።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው፤ የመረጃ ስርአቱን ፈጣን፣ ትክክለኛና ተአማኒነት ያለው ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ ይገባል ብለዋል።  

አራተኛው የመረጃ ነጻነት ቀን በማስመልከት የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ የተለያዩ ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች፣ ምሁራንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም