የጉለሌና ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተሞች ለመከላከያ ሠራዊት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

164

ኅዳር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጉለሌና ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተሞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት በገንዘብና በአይነት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለጸ።

በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ የደም ልገሳ ተካሂዷል።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት በገንዘብና በአይነት 31 ሚሊዮን 165 ሺህ ብር ድጋፍና የስንቅ ዝግጅት አድርጓል።

ክፍለ ከተማው እስካሁን 157 ሚሊዮን 365 ሺህ ብር ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጉን የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሰራዊት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ክፍለ ከተማው ድጋፉን ያደረገው ከነዋሪዎቹ በማሰባሰብ ሲሆን፤ ድጋፉን የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ነጻነት ዳባ ለመከላከያ ሰራዊቱ ተወካይ ኮሎኔል ሌቺሳ መገርሳ አስረክበዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ለሰራዊቱ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ በቀጣይም ይህን ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ሰራዊቱን ወክለው ድጋፉን የተቀበሉት ኮሎኔል ሌቺሳ መገርሳ በበኩላቸው “እየተደረገልን ያለው ድጋፍ ግዳጃችንን በድል ለማጠናቀቅ የሞራል መነሳሳት ፈጥሮልናል” ብለዋል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ላደረገው ድጋፍም በሰራዊቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።