ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በአየርላንድ ተካሄደ

66

ህዳር 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በአየርላንድ መዲና ደብሊን ተካሄደ።

ሰልፉ 'ደብሊን ሲቲ ሴንተር' እየተባለ በሚጠራ አካባቢ ነው የተከናወነው።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በአየርላንድ ደብሊን፣ ኮርክ፣ ጋሎዌይና ሌሎች ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም የአየርላንድ ዜጎች መሳተፋቸውን 'ቮይስ ፎር ኢትዮጵያ አየርላንድ' የተሰኘው ግብረ ሃይል አባል ወይዘሮ ራሔል ዳልተን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያን እንደማይቀበሉና እጃቸውን እንዲያነሱ ሰልፈኞቹ ማቅረባቸውን አመልክተዋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች  የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን ተገቢ ያልሆነና ለአንድ ወገን ያደላ አቋም ማስተካከያ እንዲያደርግ ጥሪ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

የአየርላንድ በተለይም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይሞን ኮቬኔይ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚሰጧቸው አስተያያቶች የተሳሳቱና ሊታረሙ የሚገባቸው መሆኑን ሰልፈኞቹ መግለጻቸውን ነው ወይዘሮ ራሔል ያነሱት።

ሰልፈኞቹ  የአየርላንድ መገናኛ ብዙሃን በተለይም 'አርቲኢ ኒውስ' እና 'አይሪሽ ታይምስ' በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚያወጧቸውን አፍራሽና አድሏዊ ዘገባዎችን ማውገዛቸውንና ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ ማስተላለፋቸውንም ገልጸዋል።

በሰልፉ 'በቃ' ወይም '#NoMore' መፈክሮች መስተጋባታቸውንና በአየርላንድ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መሆናቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ በአየርላንድ የሚኖሩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ ለማዘጋጀት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

ከሰልፉ ባለፈ ለአየርላንድ ባለስልጣናት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የማስረዳትና ለፓርማላ አባላት ደብዳቤ በመጻፍ የመሞገት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ወይዘሮ ራሔል የተናገሩት።

በቅርቡም ዳያስፖራው ከ100 በላይ ለሚሆኑ የአየርላንድ ፓርላማ አባላት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ደብዳቤ ማስገባቱን አስታውሰዋል።

በአየርላንድ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ኢትዮጵያያን ለመደገፍ ከምንጊዜውም በላይ  ዝግጁ መሆናቸውን አክለዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሕዳር 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከተልዕኳቸው ውጭ ሲንቀሳቀሱ ያገኛቸውን አራት የአየርላንድ ዲፕሎማቶች በሳምንት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑ ይታወሳል።

በተመሳሳይ ትናንት በደቡብ ኮሪያ ሴኡል፣ በኖርዌይ ኦስሎና በጣልያን ሚላን ከተሞች ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና የሚቃወም ሰልፍ መካሄዱ ይታወቃል።

በተያያዘም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ላይ የምታደርገውን ጫና የሚቃወም ሰልፍ ዛሬ በኢትዮጵያሰዓት አቆጣጣር ከምሽቱ ሰዓት በዋሺንግተን ዲሲ ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት ይካሄዳል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም