ኢትዮጵያ ምን አይነት ዲፕሎማሲ ያሻታል?

123

ህዳር 19/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ምን አይነት ዲፕሎማሲ ያሻታል?
ኢትዮጵያ በታሪክ ቅኝ ግዛት አለመያዟ በነጭ ቅኝ ግዥዎች ጥርስ ውስጥ እንዳስገባት ሁሉ ለጥቁሮች ደግሞ የነጻነት እና የትግል ፋና ወጊ እንደሆነች አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ይናገራሉ።

በተለይም ድሕረ አድዋ ድል ኢትዮጵያዊነት በባርነት ውስጥ ለነበሩ የዓለም ጥቁሮች ሁሉ ማታገያ ትዕምርት እንደሆነ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ በኢትዮጵያ ስም የተቋቋሙ ተቋማት ዛሬም ሕያው ማሳያ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ጥቁሮች በቅኝ ግዛት ያጡት ስልጣኔ መዘክር መሆኗን አፍሪካዊያን እንደሚያውቁ ገልጸው፤ በአንጻሩ ይህን መልካም የዲፕሎማሲ መንገድ ኢትዮጵያ አልተራመደችበትም ይላሉ።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የጋራ ስልጣኔና ማንነት የጠበቀች አገር መሆኗን በማስገንዘብ ከአፍሪካዊያን ጋር አብሮ መሰለፍ የወቅቱ አንኳር የዲፕሎማሲ አማራጭ መሆኑን አምባሳደር ጥሩነህ ገልጸዋል።

ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ህዝብ ባላት አፍሪካ የትብብር ግንኙነቱ ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይገባዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ ስትወረር በማይጨው ግንባር የተዋጉትን ኮሎል ጆን ሮቢንሰን ጨምሮ ጥቁር አሜሪካዊያን ከኢትዮጵያ የውስጥ ጠላቶች ጋር መዋጋታቸውን አውስተዋል።

በዶክተር መላኩ በያን አሰባሳቢነትም ጥቁር አሜሪካዊያን በአሜሪካ የኢትዮጵያን ማህበር አቋቁመው ገንዘብ በማሰባሰብ ከኢትዮጵያ ጐን ተሰልፈው እንደነበርም ያስታውሳሉ።

ይህ ታሪካቸው ሳይዘነጋ ይልቁንም አብሮነትንና ትብብርን ዳግም አድሶ በተለይም ጥቁር አሜሪካዊያንን ከኢትዮጵያ ጎን ማሰለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በርካታ የአፍሪካ አገራት ከጥቁር አሜሪካዊያን ጋር የተሳሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ይህን ሊከተሉ ይገባል ነው ያሉት።  

ዓለም ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በፊት በሁለት ሃይላት ጎራ ስትመራ ብትቆይም ዛሬ ላይ ግን በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ የዳበሩ አያሌ ሃይላት እንደተፈጠሩ ይገልጻሉ።

ለአብነትም የዛሬ 60 ዓመት 60 በመቶ የዓለማችን ኢኮኖሚ ምርት በአሜሪካዊያን ዕጅ የነበረ ሲሆን ዛሬ ግን 21 በመቶ ብቻ ድርሻ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያን ከድህነት ማውጣት ላይ በማተኮር ዲፕሎማሲያችን የትኛው አገር የተሻለ ጥቅም ይሰጠኛል የሚለው መታየት ይኖርበታልም ነው ያሉት።

ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት በቻይና በዋሻ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ አስታውሰው አሁን ላይ በወቅቱ ከነበረው 200 ሚሊየን ገዳማ ደሃ ህዝብ ቻይና ጠንክራ በመስራቷ ሁሉንም ከድህነት አላቃለች ብለዋል።

ኢትዮጵያም ይህን ለመስራት የህዝቡን ሕይወት መለውጥ የሚያስችሉ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎችን መተግበር፣ ከአንድ ወገን ላይ ከመንጠልጠል ከተለያዩ አገሮች ጋር መተባበር እንዳለባት ይመክራሉ።

ከኢትዮጵያ የረጂም ጊዚ ታሪክ ለሕልውናዋ በየዘመኑ ውለታ የዋሉላት ወዳጅ አገራትን የማመስገንና ወዳጅነትን የማስቀጠል ባህል ሊዳብር ይገባልም ነው ያሉት።

በሊግ ኦፍ ኔሽን ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት እንዳልሆነች የመሰከረችውን ሩሲያን ጠቅሰው በጸጥታው ምክር ቤት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ማእቀብ ለመጣል ያደረገችውን ሙከራ ሩሲያ በመቃወም የኢትዮጵያ ቋሚ ወዳጅ መሆኗን አሳይታለች ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ህዝብ በየዘመናቱ የተፈተነ በመጥፎ ጊዜ እንድ ሆኖ የተሻገረ፣ ፋሽዝምን ያለፈ ጠንካራ ህዝብ በመሆኑ አሁንም በድል ይወጣዋል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም