የምሥራቅ ወለጋ ዞንና የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ወደ ግንባር ለመዝመት ተዘጋጁ

ነቀምቴ፤ ህዳር 19/2014(ኢዜአ) የምስራቅ ወለጋ ዞንና የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርአያነት በመከተል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ወደግንባር ለመዝመት መዘጋጀታቸው ተገለጸ።
የብልጽግና ፓርቲ የምሥራቅ ወለጋ ዞን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ዴሬሣ፤ የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ሀገር የማፍረስ ዓላማን ለማክሸፍ የሁሉም ህብረትና አንድነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ "ግንባር ላይ እንገናኝ "ብለው አሸባሪውን ሀወሓት ለመፋለም መዝመታቸው በዞኑ አመራሮች ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን እንደፈጠረም ገልጸዋል።

አቶ ዓለማየሁ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በዞን እና በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮች ወደ ትግሉ ጎራ ለመቀላቀል ተመዝግበው በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

"እኔም አብሬ ለመዝመት ዝግጅቴን ጨርሼያለሁ" ብለዋል፡፡

የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቶሌራ ረጋሣ በበኩላቸው፤ ሀገርን ለማዳን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደግንባር መዝመት ለእሳቸው ብርታት እንደሆናቸው ይናገራሉ።

እስከዛሬ ለህልውና ዘመቻው በተለያየ መንገድ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩ አስታውሰው፤ አሁንም ግንባር ድረስ ዘምተው ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ አሸባሪዎቹ ሕወሓትንና ሸኔን ለመፋለም መነሳታቸውን አስታውቀዋል።  

በከተማ አስተዳደሩ እሳቸውን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ  አመራሮች ተመዝግበው ወደግንባር ለመዝመት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውንም ከንቲባ ቶሌራ አስታውቀዋል፡፡

ከሀዲዎች ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብረው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በለኮሱት ጦርነት በርካታ ንጹሀን ከመሞታቸው ባለፈ በሀገር ሀብት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰዋል።

"የእነዚህን ባንዳዎች ከንቱ ምኞት እንዳይሳካ ማድረግ የሚቻለው ሁላችንም የድርሻችንን ማበርከት ስንችል ነው" ያሉት አቶ ቶሌራ፤ አመራሩ ለመዝመት ቆርጦ የተነሳው ኢትዮጵያን ከእነዚህ አጥፊዎች ለመታደግ በሚደረገው ጥረት የድርሻውን ለመወጣት መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አመራር የዶክተር አብይን ምሳሌነት በመከተል ወደግንባር ለመዝመት መመዝገባቸውን የገለጹት ደግሞ የምሥራቅ ወለጋ ዞን  የአስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦልጅራ በየነ ናቸው።

"የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንባር ተጋድሎ የትግሉን ሜዳ ለመቀላቀል አነሳስቶኛል" ያሉት ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት ለእናት ሀገራቸው ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ከሌሎች አመራሮች ጋር ሆነው ተነሱ የሚል ጥሪ እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ  ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደረጄ አበራ በበኩላቸው፤ በዞን ደረጃ የሚገኙ አመራሮች በህልውና ዘመቻው ሀገር እንድታሸንፍ የበኩላቸውን እገዛ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።     

"በአሁኑ ወቅትም በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ፈለግ በመከተል ቤቴ፣ ህብቴ እና ንብረቴ ሳይሉ ለመዝመት በከፍተኛ ወኔ ተነሳስተዋል" ነው ያሉት።

አመራሩ ሀገርን ለማዋረድ የተነሱት  አሸባሪዎቹን ሕወሓት እና ሸኔን ለመፋለም በቁርጠኝነት መነሳቱንም ነው አቶ ደረጄ የገለጹት።

ሀገር ሉአላዊነቷና ክብሯ ተጠብቆ እንድትቆይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ፈለግ ተከትለው ከሚዘምቱት የዞኑ አመራሮች ጋር አብረው ለመሄድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ምክትል አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም