በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ የተቀናጀ ስራ ጀምረናል

88

ህዳር 19/2014 /ኢዜአ/ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ የተቀናጀ ስራ መጀመራቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።
በአሜሪካ 500 ሺህ የሚሆኑ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊያን እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙ ሰልፎች ከሰሞኑ በአገሪቷ የተለያዩ ከተሞች መካሄዳቸው ይታወቃል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራው በአሜሪካ ፖለቲካ ላይ ያለው  ተሳትፎ በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በአሜሪካ ካሊፎሮኒያ ነዋሪ ውኢንጂነር በሃይሉ አሰፋ  ና አቶ አቢይ ገብረሕይወት በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ነዋሪ እንዲሁም በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ነዋሪ አቶ አለማየሁ አበበ እንዳሉት አሜሪካ ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለች ያለው ፖሊሲና የምታደርገው ጫና የዳያስፖራውን ማህበረሰብ ወደ ፖለቲካና ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ መግባት እንዳለበት ያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሰላማዊ ሰልፎችን በማድረግ የተጀመረው ጥረት ወደ ተደራጀ እንቅስቃሴ መሸጋገሩንም አመልክተዋል።

በቅርቡ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ትውልደ-ኢትዮጵያውያንን በመቀስቀስ በቨርጂኒያና በጆርጂያ ግዛቶች በተደረጉ ምርጫዎች ለሪፐብሊካን ፓርቲ እጩዎች ድምጽ በመስጠት የዴሞክራት ፓርቲ ተወዳዳሪዎች እንዲሸነፉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ምርጫው ዴሞክራቶች ኢትዮጵያን የሚጎዳ ፖሊሲ መከተላችሁ ዋጋ እንዳስከፈላቸውና በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና እስኪቆም እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መልዕክት ያስተላለፈ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች በሚካሄዱ የአካባቢና የአጋማሽ ዓመት  ምርጫዎች ላይ ትውልደ-ኢትዮጵያኑ ኢትዮጵያንና ዳያስፖራውን ጥቅም ሊያስከብሩ ለሚችሉ እጩዎች ድምጻቸውን እንዲሰጡ ቅስቀሳ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከምርጫው ባለፈ የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲከበር አግባቢዎችን( ሎቢስት) በመቅጠር፣ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በማከናወን እና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችና ጥምረቶች በመቋቋም የተለያዩ ተግባራትን እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የዳያስፖራው ተሳትፎ ሴናተር እና የኮንግረስ አባል ሆኖ የኢትዮጵያን ድምጽ እስከ ማሰማት ግብ እንዳለውና ይሄም ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እየተሰራበት እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በአሜሪካ የሚኖረው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ኢትዮጵያን በገንዘቡ፣በእውቀቱና ባለው የተለያየ አቅም ለመደገፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ ሆኖ መነሳቱንም አምባሳደር በፍቃዱ ረታ በአሜሪካ ቺካጎ ነዋሪ ና አቶ አቢይ ገብረሕይወት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለመደገፍ መንግስት ከዳያስፖራው ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባው ገልጸው፤ በአጭር ጊዜ ውሰጥ ሰላም በማምጣት ኢትዮጵያን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለስ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ሳምራ ብሩክ እ.አ.አ በ2020 የዴሞክራት ፓርቲ እጩ በመሆን በአሜሪካ ኒው ዮርክ ግዛት በተካሄደው የሴናተርነት ምርጫ  የሪፐብሊካኑን እጩ ክርስቶፈር ሚሲክን በማሸነፍ በኒው ዮክ የመጀመሪያ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ ሴት የሴኔት አባል መሆኗ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ እ.አ.አ በ2020 በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የኦስቲን ምክር ቤት አባል ለመሆን በተካሄደ ምርጫ ኦባላ ኦባላ ዴሞክራት ፓርቲን ወክሎ ተፎካካሪውን ሄለን ጃርን በማሸነፍ በ152 ዓመታት የምክር ቤቱ ታሪክ የመጀመሪያው ትውልደ-ኢትዮጵያዊ አባል መሆን መቻሉ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም