በምሳሌነት ሲጠቀሱ የነበሩት አንዳንድ የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች የጥፋትና የውሸት ምሳሌ እየሆኑ ነው

109

ህዳር 19/2014/ኢዜአ/ በጋዜጠኝነት ትምህርት በምሳሌነት ሲጠቀሱ የነበሩት አንዳንድ የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች የጥፋትና የውሸት መገለጫዎች መሆናቸውን በግልጽ እየታዘብናቸው መጥተናል ሲሉ የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

አሜሪካና አንዳንድ የምዕራቡ አለም ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ያለውን አውነታ በካደ መልኩ የሃሰትና ፍፁም ወገናዊነት የሚታይበት ዘገባ ማሰራጨቱን ተያይዘውታል።

መገናኛ ብዙሃኑ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን እንዳይረዳ በማሳሳት በኢትዮጵያ ላይ የተዛባ ምልከታ እንዲኖር እየሰሩም ይገኛሉ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን መምህር ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ፤ በጋዜጠኝነት ትምህርት በምሳሌነት ይጠቀሱ የነበሩት በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የጥፋትና የውሸት መገለጫዎች መሆናቸውን በግልጽ እየታዘብናቸው መጥተናል ብለዋል።

ከጋዜጠኝነት ስነ ምግባር መርህ ይልቅ ለቆሙለት አላማ በወገናዊነት እየሰሩ በመሆኑ "ሁላችንም ለምን ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል" ነው ያሉት ዶክተር ደመላሽ።

በዩኒቨርሲቲው የሚዲያና ኮሚኒኬሽን መምህር  ዶክተር ጌታቸው ጥላሁን በበኩላቸው የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎች "እኛን የጋዜጠኝነት ሙያዊ ስነ ምግባር እያስተማሩ እነርሱ ግን በተግባር ተቃራኒ መሆናቸውን ታዝበናቸዋል" ብለዋል።

በጋዜጠኝነት ሙያ በምሳሌነት እየጠቀስናቸው መማሪያና ማስተማሪያ ያደረግናቸው አንዳንድ የምእራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን ለሙያቸው ሳይሆን ለቆሙለት ዓላማ እየሰሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ጌታቸው " የአገራችን ሚዲያዎችም ኢትዮጵያንና ህዝቧን አስቀድመው ሊሰሩ ይገባቸዋል" ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም