ዳያስፖራው ለሀገር ሉዓላዊነትና ነፃነት እየተፋሉ ላሉት የፀጥታ ኃይሎች ታላቅ አክብሮት እንዳለው ተገለጸ

65

ጎንደር፤ ህዳር 18/2014(ኢዜአ) ዳያስፖራው ለሀገር ሉዓላዊነትና ነፃነት እየተፋሉ ላሉት የፀጥታ ኃይሎች ታላቅ አክብሮት እንዳለው ተወካያቸው ገለጹ፡፡

ኑሯቸውን በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በአውስትራሊያና በእሥራኤል ያደረጉ ዳያስፖራዎች አሸባሪውን ህወሓት  ለሚፋለሙ የፀጥታ ኃይሎች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ዳያስፖራዎቹ ተወካይ ወጣት ፋሲል ይትባረክ በድጋፍ ርክክብ ሥነስርዓቱ ዳያስፖራው የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተዋደቁ ላሉት የፀጥታ ኃይሎች ክብርና አድናቆት እንዳለው ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሕልውና ዘመቻውን በግንባር መምራታቸው ቀደምት አባቶቻችን ለሀገራቸው ክብርና ነጻነት የከፈሉትን የመስዋዕትነት ታሪክ ዳግም ያደሱ ታላቅ የሀገር መሪ ናቸው ብሏል፡፡

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አገራችን ከገጠማት ፈተና እንድትሻገር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን ለማስገንዘብ ጥረት እያደረጉ  መሆናቸውን ተወካዩ አመልክቷል።

ዲያስፖራዎቹ ካደረጉት ድጋፍ መካከል ቴምር፣ ብስኩት፣50 ኩንታል የጤፍ ዱቄት፣ አልባሳትና ጫማ ይገኙባቸዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው ዳያስፖራው ለህልውና ዘመቻው መሳካት እያደረጉት ያለው ድጋፍ ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን በተግባር አረጋግጧል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የውጭ ኃይሎች ጫናና ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ለመመከት ዲያስፖራው ማህብረሰብ በዓለም አቀፍ መድረኮች እያደረገ ያለው የነቃ ተሳትፎ አድንቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም