በአሸባሪው ቡድን ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ለተጠለሉ ወገኖች ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

215

ደብረ ብርሃን ፤ህደር 18/2014 (ኢዜአ)የቤኒሻንጉን ጉሙዝ ክልል ነጋዴ ማህበረሰብና ሴት ጋዜጠኞች በአሸባሪው ህወሃት ቡድን ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ለተጠለሉ ወገኖች ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብ ነክ ድጋፍ አደረጉ።

የቤኒሻንጉን ጉሙዝ  ክልል ነጋዴ ማህበረሰብ  ተወካይ ሼህ እንድሪስ አህመድ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ከጥፋት ሀይሎቹ ለመታደግ የጋራ ትብብር ያስፈልጋል።

የክልሉ ነጋዴ ማህበረሰብ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናሉ ወገኖች እንዲውል 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው 450 ኩንታል የዳቦ ዱቄት መለገሳቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ አምስት ሴት ጋዜጠኞች ”ለእናት ሀገር ጥሪ”  መሪ ሃሳብ በማህበራዊ የትስስር ገፆች  350 ሺህ ብር ማሰባሰብ እንደቻሉ  የድጋፍ አሰባሳቢ ቡድን አስተባባሪ ጋዜጠኛ ስመኝ ግዛው ገልጻለች።

በተሰበሰበው ገንዘብ የተዘጋጀ   በሶ  ድጋፍ መደረጉን ጠቅሳ፤ መረዳዳትና መደጋገፍ ከአባቶቻችን የወረስነው መልካም እሴት በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብላለች።

የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ  አቶ ሲሳይ ወልደ አማኑኤል፤ አሸባሪዎቹ  ህወሃትና ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጥፋት ቡድኖችን ሴራ ለማክሸፍ  ይበልጥ ተቀራርቦና ተባብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ድጋፉ ለተፈናቃይ ወገኖች እንዲደረስ እንደሚያደርጉ ገለጸዋል።