የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ለመከላከያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመድሃኒት ድጋፍ አደረገ

161

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ለመከላከያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመድሃኒት ድጋፍ አደረገ።

የተደረገው ድጋፍ በሆስፒታሉ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ለሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚውል ነው።

የተበረከተው መድሃኒት ኖርማል ሳሊን(normal salin) የተሰኘና በደም ስር የሚሰጥ ሲሆን በቀላሉ ቁስልን ለማድረቅ ያግዛል ተብሏል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሔራን ገርባ ድጋፉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት  ኢትዮጵያ ተገዳ በገባችበት የህልውና ዘመቻ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዜጎች መስእዋትነትን እየከፈሉ ይገኛሉ ብለዋል።

በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ደርሶባቸው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቶሎ አገግመው ወደ ሙሉ ጤንነታቸው እንዲመለሱ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን አንስተዋል።

በተለይ ደግሞ የጤናው ዘርፍ የህክምና ቁሳቁሶችንና መድሃኒቶችን በሚፈለገው መጠን በማቅረብ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

በዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአገር ውስጥ የመድሃኒት አምራች ድርጅቶች ጋር በመተባበር በደም ስር የሚሰጥ የቁስል ማድረቂያ መድሃኒት ለሆስፒታሉ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ አዛዠ ብርጋዴር ጄነራል ተገኝ ለታ በበኩላቸው የባለስልጣኑ መላው ሰራተኛና አጋር አካላት በሆስፒታሉ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው የሚገኙ የሰራዊቱን አባላት በመጠየቃቸው ብሎም አስፈላጊ ድጋፍ በማድረጋቸው ምስጋናን ችረዋል።

የተደረገው ድጋፍ ታካሚዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገግሙ ይረዳቸዋልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ያሬድ ሔርጶ  እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ ሰራዊቱ አገርን ለማዳን እየከፈለ ያለውን መስእዋትነት ማየት መቻላቸው ትልቅ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

በዚህ አገርን የማዳን ሂደት ውስጥ ህይወቱን እየሰጠ ያለውን የመከላከያ ሰራዊት በተለያየ መልኩ ማገዝ የግድ ያስፈልጋል ብለዋል።

የተጎዱ የሰራዊቱ አባላት ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ የመንግስት ሃላፊነት ብቻ አይደለም ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የግሉ ዘርፍም ሃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም