የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ለሠራዊቱ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ

178

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶችና የሸማች ማኅበራት ለመከላከያ ሠራዊት ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አበረከቱ፡፡

ነዋሪዎቹ፣ ባለሃብቶቹና የሸማች ማኅበራቱ ለሕልውና ዘመቻው ለ3ኛ ጊዜ ነው ድጋፍ ያደረጉት፡፡

የገንዘብና የአይነት ድጋፉ በግንባር ለተሰለፈው ሠራዊትና በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ነው፡፡

የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቆንጂት ደበሌ ነዋሪዎቹ “በአገራችን ጉዳይ ተሳታፊ እንጂ ተመልካች አይደለንም” በሚል ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም 31 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ ማበርከታቸውንና ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው  ስንቅ  እናቶች ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ቢሮ ኃላፊ ሂክማ ከይረዲን ነዋሪዎቹ የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ እያደረጉ ያሉት ተሳትፎ የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል።

በአገራችን ላይ እየተሸረበ ያለውን ሴራ ለመከላከል አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባልም ብለዋል።

በኢትዮጵያዊያን ትግል የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ሕልውና ይረጋገጣል ያሉት ደግሞ በመከላከያ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ ናቸው፡፡