ግብር በወቅቱ በመክፈልና መከላከያን በመደገፍ አጋርነታችንን በተግባር እያሳየን ነው

183

ጂንካ፤ ህዳር 18/2014 (ኢዜአ) ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል እና መከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍ ሀገራቸውን ለማዳን አጋርነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆናቸውን በደቡብ ኦሞ ዞን የጂንካ ከተማ ግብር ከፋዮች ተናገሩ።
 

በከተማዋ በሆቴልና ሱፐር ማርኬት ንግድ አገልግሎት የተሰማሩት አቶ ኤፍሬም ገዛኽኝ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ሀገር ከገጠሟት ችግሮች እንድትወጣ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ነው የገለጹት።

በየዓመቱ በወቅቱ ግብራቸውን ከመክፈል ባለፈ በግንባር እየተፋለመ ላለው የመከላከያ ሠራዊት በተለያየ መንገድ ድጋፍ  ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣውን ዘመቻ ለመመከት ለሠራዊቱ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግና ደም በመለገስ እንደ ንግድ ማህበረሰብ የበኩላቸውን ተሳትፎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

“በቀጣይም የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ የማደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

ምዕራባዊያን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዳከምና ልዑላዊነቷን ለመናድ በመገናኛ ብዙሀኖቻቸው ጭምር ሳይቀር የተደራጀ ዘመቻ መክፈታቸው እንደሚቃወሙም አመልክተዋል።

“ኢትዮጵያን በእጅ አዙር የዘመናዊ ቅኝ ግዛት ሰለባ ለማድረግ እየፈጠሩት ያለውን ጫና መመከት የምንችለው ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ስንቀሳቀስ ነው” ብለዋል አሰተያየት ሰጪው።

“ለዚህም እኔን ጨምሮ ግብር ከፋዮች በተሰማራንበት የንግድ ሥራ ግብራችንን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ሀገራዊ ሀላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል” ሲሉ አክለዋል።

ሌለው  በንግድ ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ የውብዳር ወርቁ፤ በተሰማሩበት የሆቴል አገልግሎት ሥራ ዓመታዊ ግብራቸውን በታማኝነትና ጊዜውን ጠብቀው እንደሚከፍሉ  ገልጸዋል።

“ከግብር የሚሰበሰበው ገንዘብ ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦው የጎላ በመሆኑ ግብር መክፈልን እንደ ግዴታ ሳይሆን እንደ ውዴታ ነው የማየው” ብለዋል።

ግብርን በወቅቱና በታማኝነት መክፈል በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቋቋም የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።  

መንግስት በግብር የሚሰበስበውን ገንዘብ መልሶ ለህዝብ አገልግሎት ስለሚያውለው ሁሉም ግብር ከፋዮች ያለማንም ቀስቃሽ ግብራቸውን በወቅቱ እንዲክፍሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሀገር አሁን ከገጠማት የህልውና አደጋ ፈጥና በመውጣት ልማቷን እንድታስቀጥል ለመከላከያ ሠራዊት የጀመሩትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩም ወይዘሮ የውብዳር አስታውቀዋል።  

የደቡብ ኦሞ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በምዕራባዊያን የሚደረግባትን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም የውስጥ ገቢ አቅምን የማሳደግ ሥራ ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።

በዞኑ ከሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ.ም የግብር አሰባሰብ ንቅናቄ ተደርጓል ነው ያሉት።

በነዚህ ጊዜያትም  በዞኑ ከሚገኙ ከ10ሺህ በላይ የደረጃ ”ሀ”፣ ”ለ” እና ”ሐ” ግብር ከፋዮች 34 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ መከናወኑን ተናግረዋል።

የዞኑ ግብር ከፋዮች ሀገር የሀገርን ችግር በመረዳት ግብራቸውን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈላቸው ከዕቅድ በላይ ሊሰበሰብ እንደቻሉ ሀላፊው አመላክተዋል።