ጦርነቱ በአሸናፊነት ተጠናቆ ዳግም የአድዋ ታሪክ ይሰራል

190

ሚዛን አማን ፤ ህዳር 18/2014 (ኢዜአ) በምዕራባውያን የሚደገፈው አሸባሪው የህውሃት ቡድን የከፈተብንን ጦርነት በአሸናፊነት በማጠናቀቅ ዳግም የአድዋ ታሪክ ይሰራል ይላሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ።

ዩኒቨርሲቲው ሰራተኞቹን በማስተባበር ለመከላከያ ሰራዊት የሚሆን ስንቅ እያዘጋጀ ነው።

በወቅታዊ ጉዳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንዳሉት፤ ጦርነቱ የአድዋ ዓይነት ታሪክ የሚሰራበት ነው።

በምዕራባዊያን ተደግፎ ሀገር የማፍረስ ዓላማ ይዞ የመጣውን የአሸባሪ ቡድን ለመፋለም  በግንባር ከመዝመት ባሻገር ስንቅ በማቀበል ሁሉም ዜጋ እየተሳተፈበት እንደሚገኝ በግልጽ እንደሚታወቅ ጠቅሰዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲም ሀገራዊ ግዴታውን ለመወጣት ለመከላከያ ሰራዊት ስንቅና ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚሆን የድጋፍ ቁሳቁስ እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጦርነቱ አሸባሪው ህወሃት  ጋር ብቻ አለመሆኑን የገለጹት ዶክተር  አህመድ ፤ በእጅ አዙር እየተዋጉ ያሉ ምዕራባውያን መኖራቸውን አንስተዋል።

“ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በታርኳ ሽንፈት የማታውቅ በመሆኗ ጦርነቱ በአሸናፊነት ተጠናቆ ዳግም የአድዋ ታሪክ ይሰራል” ነው ያሉት።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  አህመድ ወደ ጦር ግንባር መምራታቸው ኢትዮጵያ መቼውም ለጠላት የማትንበረከክ መሆኗን ለጠላቶቿ የሚያረጋግጥ እንደሆነም ገልጸዋል።

ህዝቡ ከመረጠው መንግስት ጋር ያለው ጥምረት ለጠላቶች ፈታኝ እንደሆነባቸው  ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው ለመከላከያ ሠራዊት ስንቅ እያዘጋጁ  ኢዜአ ካነጋገራቸው ሰራተኞች መካከል የተቋሙ  ባልደረባ ወይዘሮ አዳነች ንጉሴ በበኩላቸው ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት ትልቅ ወኔን እንደቀሰቀሰባቸው ገልጸዋል።

ሰራዊቱ ከስንቅ ዝግጅት ባሻገር በገንዘብና ጉልበት እየደገፉ  የራሳችንን አሻራ በማሳረፍ ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻውን እንደሚያግዙም ተናግረዋል።

ሌላዋ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኛ ወይዘሮ የምስራች ዘለቀ፤  የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብለን ባለን ሁሉ መከላከያን መደገፍ አለብን ብለዋል።

ደም መለገስ፣ ስንቅ ማዘጋጀትና ማቀበል ጦርነቱ የተቀላጠፈ እንዲሆን ያግዛል ነው ያሉት።

ሌላው በስንቅ ዝግጅቱ እየተሳተፉ ያለው ወይዘሮ  መቅደስ ብላታ በበኩላቸው፤ ወደ ግንባር ቢሄዱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ እና መከላከያ ሰራዊት ስንቅ ማዘጋጀት ትልቅ ነገር አለመሆኑን ጠቅሰው “እኔ በበኩሌ ህይወት ለመስጠት ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።

በየትኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።