አሸባሪው ህወሓት በካሳጊታ እና ሙዴና ከተሞች በወገን ጦር ተመቶ ከመሸሹ በፊት ሴቶችና ሕፃናትን ጨፍጭፏል፥ ንብረትም አውድሟል

65

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ በአፋር ክልል ካሳጊታ እና ሙዲና ከተሞች በወገን ጦር ተመትቶ ከመሸሹ በፊት በርካታ ሕጻናትና ሴቶችን ጨፍጭፏል፤ ንብረትም አውድሟል፡፡

በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መላው የጸጥታ ኃይል በካሳጊታ ግንባር አሸባሪው ህወሃትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ስትራቴጂካዊ ስፍራዎችን ማስለቀቁ ይታወቃል፡፡

የጸጥታ ሃይሉ ቡርቃንና በባቲ ከተማ ዙሪያ ያሉ ተራሮችን ተቆጣጥሮ ወደ ባቲ ኮምቦልቻ እየገሠገሠ መሆኑንም ትናንት ማምሻውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጹ ይታወሳል፡፡

ምንጮቻችን ከስፍራው እንደገለጹት፤ አሸባሪ ቡድኑ በካሳጊታ እና ሙዲና ከተሞች የወገን ጦርን መቋቋም አቅቶት ከመሸሹ በፊት በርካታ ህጻናትንና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ አቅመ ደካሞችን ጨፍጭፏል፡፡

መስጂዶችን አውድሟል፤ ቁራዓን ሰብስቦ አቃጥሏል፡፡

የዜጎች ጥሪቶች የሆኑ ቤቶች፣ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በከባድ መሳሪያ በመምታትና በእሳት በማቃጠል አውድሟል።

አሸባሪ ቡድኑ የዜጎችን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ መሰረተ ልማቶች በማውደም ለሰው ልጆች የማይበጅ አረመኔያዊ ቡድን መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ኃይል በወገን ጦር እየደረሰበት ያለውን ምት መቋቋም አቅቶት የያዘውን ሁሉ እያዝረከረከ በመፈርጠጥ ላይ ይገኛል።

መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ በሰጠው መግለጫ ሽንፈት ገጥሞት በመፈርጠጥ ላይ የሚገኘው የአሸባሪው ህወሃት ቡድን እያወደመና እየዘረፈ እንዳይሄድ ህብረተሰቡ አካባቢውን እንዲጠብቅ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም