ወራሪ ኃይሉን በመመከትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ማክሸፍ አለብን

69

አዳማ፣ ህዳር 18/2014/ኢዜአ/ 16ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ስናከብር ወራሪ ኃይሉን በመመከትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ማክሸፍ አለብን ስሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ገለፁ።

በዓሉ "ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በመጪው ህዳር 29 በድሬደዋ ይከበራል።

ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዘሃራ አህመድ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት ብሔር ብሐረሰቦችና ህዝቦች ወራሪውን ኃይል በጋራ እየመከቱና የውጭ ጣልቃ ገብነት ይብቃን በማለት ለሀገራቸው ዘብ ቆመዋል።

የኢትዮጵያዊንን የሀገር ፍቅር በበለጠ ያነሳሳው የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የግንባር ዘመቻ አሁንም በህዝብ ማዕበል ታጅቦና ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዕርዳታ ስም የውጭ ጣልቃ ገብነትና የእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ እንደማንቀበል ሁላችንም በአንድነት ቆመን መታገል አለብን በዚህም ዳግማዊ አድዋን እውን እናደርጋለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባለ ብዙ ማንነት ባለቤት ብትሆንም በበቂ ሁኔታ ብዝሃነትን ማስተናገድ አልቻለችም ነበር ያሉት ደግሞ በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የህግ አማካሪ ዶክተር ዘለቀ ተመስገን ናቸው።

ለማንነቶች ህገ መንግሥቱ ዕውቅና ሰጥቷል ያሉት ዶክተር ዘለቀ ባለፉት 27 ዓመታት የብሔረሰቦች መብት ሳይሸራረፍ ከማክበርና ከማስከበር ይልቅ የአንድ የፖለቲካ ቡድን የበላይነት የተስተናገደበት ነበር ብለዋል።

ሆኖም ባለፉት ሶስት ዓመታት የህዝቦች ማንነት በትክክል የተስተናገደበት አጋጣሚዎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።

ህገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ነው ያሉት አማካሪው ዘላቂ ሰላም ፣ ልማትና ዕድገት እንዲረጋገጥ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማ ያለው ሰነድ ነው።

ለብሔሮች ብሔረሰቦች ሉዓላዊነትና ማንነት ዋስትና የሰጠ በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሀገር ህልውናን ለመታደግ በአንድነት እንዲነሱ ማስቻሉንም አመልክተዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አትፈርስም በማለት አሸባሪው ቡድን ለመደምሰስ በአንድነት እየተዋደቁ ያሉት  ህገ መንግሥቱ በሰጠው የጋራ እሴት መሆኑንም ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ ዛሬ በተካሄደው መድረክ ላይ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች የተወጣጡ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም