ታሪክ አድዋን እንደ ዘከረው ሁሉ ድሉን ለመድገም ወጣቱ በህብረት ሊነሳ ይገባል

174

ጎንደር ፣ህዳር 18/2014(ኢዜአ) ታሪክ አድዋን እንደ ዘከረው ሁሉ የምዕራባውያን ተላላኪ የሆነውን የህወሃት የሽብር ቡድን በመደምሰስ ዛሬም እንደ ትናንቱ ወጣቱ ድሉን ለመድገም በህብረት ሊነሳ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ያዘጋጀው ሀገርን የመታደግ የወጣቶች የንቅናቄና የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤  ዘመናዊ ቅኝ ግዛትን ሊጭኑብን የሚፈልጉ ምዕራባዊያን ከሃዲውን የህወሃት የሽብር ቡድን በመሳሪያነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ብለዋል።

ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት በማሰብ ወረራ በፈጸሙበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶች በፈጸሙት አኩሪ   ተጋድሎ የዛሬው ትውልድ በነጻነት እንዲኖር አስችለውታል፡፡

ታሪክ አድዋን እንደ ዘከረው ሁሉ የምዕራባውያን ተላላኪ የሆነውን የህወሃት የሽብር ቡድን በመደምሰስ ዛሬም እንደ ትናንቱ ወጣቱ ድሉን ለመድገም በህብረት ሊነሳ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሽብር ቡድኑ በወረራ በያዛቸው የአማራ አካባቢዎች ዛሬም በርካታ ህዝቦች ለችግር መጋለጣቸውን  ጠቁመው፤ ወጣቱ ሰራዊቱን በመቀላቀል ወገኖቹንና ሀገሩን ፈጥኖ ነጻ ሊያወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

''ወጣትነት ሀገርን የማዳን አቅምና ችሎታ እንዲሁም ወኔና ሀገራዊ ስሜት የሚንጸባረቅበት የእድሜ ክልል ነው'' ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ናቸው፡፡

ሀገራዊ ለውጡ ከዳር እስከ ዳር እንዲቀጣጠል ካደረጉ ግንባር ቀደም የህብረሰብ ክፍሎች አንዱ ወጣቱ በመሆኑ ዛሬም የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ሀገርን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሴራ ለመቀልበስ የወጣቱ ሚና የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካካል ወጣት የሺወንድም አምላኩ በበኩሉ፤የአሸባሪው  ህወሃት ሴራን በሚገባ የተገነዘብን በመሆኑ ወራሪውን ለመደምሰስ ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲል ገልጿል፡፡

እኛ ወጣቶች ቀስቃሽ የምንፈልግበት ጊዜ ላይ አይደለንም፤ ይልቁንም የጠላትን አፍራሽ ዓላማና የጭካኔ ድርጊት የተገነዘብን በመሆኑ ግብአተ መሬቱን ለማፋጠን ከመንግስትና ህዝባችን ጎን ቆመናል ያለው ደግሞ ወጣት ኑርሁሴን አብደላ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም