በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ያዘጋጁት ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ

73

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ አካሄዱ።

በሰልፉ ላይ ከኦስሎ፣በርገን፣ስታቫንገር፣ትሮንዳይምና ሌሎች የኖርዌይ ከተሞች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ በአገሪቷ የሚኖሩ የአፍሪካ አገራት ዜጎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፈዋል።

ሰልፉኞቹ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ "ሴንትራል ስቴሽን" እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ተነስተው ወደ አገሪቷ ፓርላማ በመሄድ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

"ምዕራባውያን አገራት ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ"፤ "ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ የሚሰሩትን የሀሰት ዘገባ ያቁሙ፣"የኢትዮጵያ ችግር በኢትዮጵያውያን ይፈታል፣"ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" እና በቃ(#Nomore) የሚሉ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ ተላልፈዋል።

በተለይም በሰልፉ ላይ "የበቃ" ወይም #Nomore" መልዕክቶች በሰፊው ተስተጋብቷል።

በሰልፉ ላይ የተሳተፉ በኖርዌይ የሚኖሩ የአፍሪካ አገራት ተወላጆች መላው አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነው፤አጋርነታችንን ለኢትዮጵያ ልናሳይ ይገባል ብለዋል።

አፍሪካውያኖች የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም እንዳላቸውና አፍሪካ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል አመልክተዋል።

አፍሪካውያን በጋራ በመቆም ምዕራባውያን ለመጫን የሚፈልጉትን የኒኦ-ኮሎኒያሊዝም አስተሳሰብ መታገል እንዳለባቸው ነው በሰልፉ ላይ የተሳተፉት የአፍሪካ አገራት ዜጎች የገለጹት።

በኖርዌይ መዲና ኦስሎ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጁት በኖርዌይ የሚገኙ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሲቪክ ማህበራት በጋራ በመሆን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም