ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው አደንዛዥ ዕፅ ከተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ዋለ

65

ድሬዳዋ፤ ህዳር 18/2014(ኢዜአ) ለሽብር ተግባር ሊውል የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው አደንዛዥ ዕፅ ከተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኮሚቴው አባል የሆነው የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የመልካጀብዱ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ኢንስፔክተር ሻንበል ተካልኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አደንዛዥ ዕፁ የተገኘው ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ መልካጀብዱ ልዩ ቦታው ገንደሁርሶ ቀበሌ ከአንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ ነው፡፡

በህዝቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር የዋለው አደንዛዥ ዕፁ በድሬዳዋና ምስራቅ ሐረርጌ ለሽብር ተግባር ለማዋል የታሰበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ለሽብር ተግባር አደንዛዥ ዕፅን ወጣቱ እንዲጠቀምበት ለማድረግ ቢሆንም በመቆጣጠር ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከጉዳዩ ጋር የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር ውለው  ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ሌላም በአስተዳደሩ በተደረገ ጥብቅ ቁጥጥር በመልካጀብዱ ቀበሌ ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች፣ የአሸባሪዎቹ ህወሃትና  የሸኔ  ተላላኪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢንስፔክተር ሻንበል ጠቁመዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አባል የሆነው የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የለውጥ ሥራዎችና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ በበኩላቸው፤ አሸባሪዎቹ ለጥፋት ተልዕኳቸው ማስፈጸሚያነት ወጣቱን ለመጠቀም የሚሞክሩት አንዱ መንገዱ አደንዛዥ ዕፅ በመስጠት አሳስተው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮሚቴ አባል በሆነው ፖሊስና ህብረተሰቡ ቅንጅት በቁጥጥር ስር የዋለው ከፍተኛ መጠን ያለው አደንዛዥ ዕፁ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ለሽብር ተግባር ለማዋል እንዳዘጋጁት ተጠርጥረው  በቁጥጥር ስር በዋሉት ሰዎች ላይ  እየተካሄደ ያለው ምርመራ  ሲጠናቀቅ ውጤቱ ለህዝቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ህብረተሰቡና ፖሊስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተው እያከናወኑት ያለው አኩሪ የደጀንነት ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም