የጋምቤላ ወጣቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተከትለው ዘመቻውን ለመቀላቀል ወሰኑ

99

ጋምቤላ፤ ህዳር 18/2014(ኢዜአ) የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስተላለፉትን "ግንባር ላይ እንገናኝ" መልዕክት ተቀብለው የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል መወሰናቸውን የጋምቤላ ከተማ  ወጣቶች አስታወቁ።

አሸባሪው የህወሓት  ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ለመቀልበስ በቁርጠኝነት መነሳታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪ ወጣቶች  ገልጸዋል።

ከወጣቶቹ መካከል  አባንግ ኮመዳን እንዳለችው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ወኔና ስሜት አነሳስቷት ሀገርን በማዳኑ ዘመቻ  ለመቀላቀል እንድትወስን አስችሏታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ ያደረጉት ዘመቻ  አፄ ምኒልክ የውጭ ወራሪን አሳፍረው ለመመለስ የፈጸሙትን የታሪክ ገደል የደገመ መሆኑን የጠቀሰችው ወጣቷ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥም የድል ባለቤት እንደሚሆኑ የጸና እምነት እንዳላት ተናግራለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉትን "ግንባር ላይ  እንገናኝ" መልዕክት  በመቀበል ዘመቻውን ተቀላቅሎ  የድርሻውን ለመወጣት መወሰኑና ለተግባራዊነቱም  ዝግጁ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ዮሴፍ  ማቲዎስ ነው።

ያለ ሀገር መኖር ስለማይቻል የህልውና ዘመቻውን በመቀላቀል አሸባሪውን የህወሓት ቡድንና ተላላኪዎቹ በመደምሰሱ ትግል ለመሳተፍ መነሳሳቱን ነው ያስታወቀው።

ወጣት ቸንኳት ዮንግ በበኩሉ ‘‘ህወሓት የሚባለው የሽብር ቡድን በሀገራችን ችግር ለመፍጠር እስከ መጣ ድረስ እንዋጋለን’’ ብሏል።

ከጥንት አባቶቻችን የወረስነውን እልህና ጀግንነት በመያዝ በጠቅላይ ሚኒስትር የተላለፈውን መልዕክት  በመቀበል የኢትዮጵያን ህልውና ለመጠበቅ ዘመቻውን ለመቀላቀል መወሰኑን የተናገረው ሌላው ወጣት  ኮር እጀሽዋ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም