በዞኑ 16 ሺህ 827 ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ላይ ስንዴን በመስኖ ማልማት ተጀመረ

226

ነቀምቴ፣ ህዳር 18/2014 /ኢዜአ/ በበጋው ወራት 16ሺህ 827 ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን በምሥራቅ ወለጋ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ዋቅጅራ ኤጀርሶ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ የተጀመረው በዞኑ በ15 ወረዳዎች ነው።

እስካሁን ባለው ሂደት 1ሺህ 60 ሄክታር ማሳ ታርሶ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

በስንዴ ልማቱ ከ 4ሺህ 240 በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ጠቁመው ከ673 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

በዘንድሮ አመት በመስኖ በስንዴ ዘር የሚሸፈነው መሬት ከባለፈው ዓመት በ11ሺህ 153 ሄክታር ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል ።

አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ በአካባቢው የሚገኙ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ በመስኖ በማልማት የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ እንዲችል እየተሰራ መሆኑን ባለሙያው አስታውቀዋል።

አርሶ አደር ፈይሣ ጅሬኛ በዞኑ የጉቶ ጊዳ ወረዳ የፈይሣ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ  በአካባቢያቸው ስንዴን በኩታ ገጠም ለማልማት የተደራጁ አርሶ አደሮች አስተባባሪም ናቸው ።

 አርሶ አደሩ እንዳሉት ዘንድሮ 75 አርሶ አደሮች በአራት ኩታ ገጠም ተደራጅተው በአሁኑ ሰዓት 20 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ሸፍነዋል።