አሳድጋና አስተምራ ለትልቅ ቦታ ያበቃችንን አገር ለማዳከም መነሳት የባንዳነት ማሳያ ነው

85

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) "አሳድጋና አስተምራ ለትልቅ ቦታ ያበቃችንን አገር ለማዳከም መነሳት የባንዳነት ማሳያ ነው" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህራን ገለጹ።

ከሰሞኑ በመቀበር ላይ የሚገኘውን አሸባሪው ህወሓትን ለመታደግ  የሽብር ቡድኑ አባላትና ምዕራባውያን የጥቅም አጋሮቹ ዲፕሎማቶች ያካሄዱት ምሥጢራዊ ስብሰባ መጋለጡ ይታወሳል፡፡

በስብሰባው ለሽብር ቡድኑ እውቅናቸውን በመጠቀም በድብቅ ድጋፍ ሲሰጡ ጭብላቸው ተገፎ በአደባባይ ከተጋለጡት መካከል ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ፣ ፕሮፌሰር ጥላሁን በየነ፣ አምባሳደር በቀለ ገለታ ዶክተር ታደሰ ወሂብ  ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

እንደ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ እና ዶክተር እሌኒ ያሉ ኢትዮጵያ አሳድጋ ለክብር ያበቃቻቸው ስመ-ጥር ሰዎች አገርን ለቀኝ ግዛትና ለዳግም ግፍ ለመዳረግ ከጀርባ ሆነው እንደሚዶልቱ በዚህ መረጃ መጋለጡ ደግሞ አግራሞትን ፈጥሯል፡፡

በዚህ ምሥጢራዊ ስብሰባ "በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስትን ልናስቆመው አንችልም የአፍሪካ ህብረት የወከላቸው የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ እኛ እንደምንፈልገው አልተንቀሳቀሱም" ማለታቸው ታውቋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የጁማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህራን እንደሚሉት፤ ግለሰቦቹ ለኢትዮጵያ አለኝታ መሆን ሲገባቸው አገርን ለውርድት ለማጋለጥ ማሴራቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡

ዶክተር ጌታቸው ጥላሁን፤ በምስጢራዊው ስብሰባ ኢትዮጵያን ይወክላሉ ብለን የምናምንባቸው ግለሰቦች በሰፈር ጨዋታ ውስጥ ተገኝተዋል ይላሉ፡፡

በመሆኑም ድርጊቱ ራሳችንን በፈተሽ ረገድ እንደ አገር ትልቅ የቤት ስራ እንዳለብን አመላካች ነው ብለዋል፡፡ 

ሌላኛው የሚዲያና ኮሚኒኬሽን መምህር ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ማዕድ ላይ ቁጭ ብለው ኢትዮጵያን ለማጥፋት እየሰሩ ያሉ ሰዎችን ማጥራት ይገባል  ነው ያሉት፡፡

አሳድጋና አስተምራ ለትልቅ ቦታ ያበቃችን አገር ለማዳከም መነሳት የባንዳነት ማሳያ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

ግለሰቦቹ ከነበራቸው ስም አንጻር የአገርን አንድነት ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መስራት ይጠበቅባቸው እንደነበርም ነው ምሁራኑ የተናገሩት፡፡

አሸባሪው ህወሃት በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ አመራጮቹን በመጠቀም ህይወቱን ለማራዘም እየተፍጨረጨረ መሆኑን ያነሱት ምሁራኑ፤ ከዚህ አኳያ ምስጢራዊው ስብሰባው የመጨረሻ አማራጩን እየተጠቀመ መሆኑን እንደሚያመላክት ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርጉትን ሴራ ነቅቶ መከታተልና ማጋለጥ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም