ቴአትር ቤቱ ሙሉ ትኩረቱን በህልውና ዘመቻው ላይ አድርጎ እየሰራ ነው

85

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ሙሉ ትኩረቱን በህልውና ዘመቻው ላይ አድርጎ እየሰራ መሆኑን የቴአትር ቤቱ አመራርና ሠራተኞች ገለፁ ።

የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ዳይሬክተር ካሣዬ ገበየሁ ለኢዜአ እንደገለፀው፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠማትን ችግር በድል እንድታልፍ ኪነ-ጥበብ የራሷን አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡

ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ የደቀነው የህልውና አደጋ ለመመከት በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ላይ ትኩረቱን አደርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

ትያትር ቤቱ በህልውና ዘመቻው በግንበር የሚሳተፉ ሰራዊቶችን የማነቃቃትና ሌሎች ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ የማነሳሳት ስራ እያከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይ የቴአትር ቤቱ የባህል ሙዚቃ ተወዛዋዥ የሆነችው  ሜሮን ወንድአፍራሽ እና ዘመናዊ ሙዚቃ ክፍል ድምፃዊ ተምቦላ አበባው፤ የትያትር ቤቱ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የህልውና ዘመቻ ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ቴአትር ቤቱ አገራዊ አንድነትን የሚፈጥሩ ጥበባዊ ዝግጅቶቹን የማቅረቡን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመራሮቹና የቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ዳይሬክትር ካሣዬ ገበየሁ  የራሳችንን ሥራ በአግባቡ መወጣት ሀገርን መጠበቅ ነው" ያለ ሲሆን ወቅታዊም ሆነ መደበኛ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብሏል።

የቴአትር ቤቱ ሙያተኞች ኅብረተሰቡን ለማስተማርና ለማነቃቃት በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተማዎች ቴአትር እየሰሩ እንደሆነም ተናግሯል።

የትያትር ቤቱ የጥበብ ባለሙያዎች በስልጠና ላይ ያሉ ምልምል ወታደሮችን የማነቃቃት ስራ እያከናወኑ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የቴአትር ቤቱ የትወና እና የተውኔት ጥበብ ቡድን መሪ መላኩ ዓለማየሁ ነው፡፡

ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስቷል፡፡

የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ሰራተኞች ከኪነ-ጥበባዊ ዝግጅት በተጨማሪ በደም ልገሳ እና  የአንድ ወር ደሞዛቸውን በመስጠት ለሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም