ሽንፈት ገጥሞት በመፈርጠጥ ላይ የሚገኘው የአሸባሪው ህወሃት ቡድን እያወደመና እየዘረፈ እንዳይሄድ ህብረተሰቡ አካባቢውን መጠበቅ አለበት

96

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሽንፈት ገጥሞት በመፈርጠጥ ላይ የሚገኘው የአሸባሪው ህወሃት ቡድን እያወደመና እየዘረፈ እንዳይሄድ ህብረተሰቡ አካባቢውን እንዲጠብቅ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር በመሰለፍ ለአገራቸው ህልውና መጠበቅ ቆራጥ መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል ነው ያሉት፡፡

ሰራዊቱና ህዝቡ በዚህ የሕልውና ዘመቻ ሞራል ማግኘቱንና የሕልውና ዘመቻውም ወደ ሙሉ ማጥቃት መሸጋገሩን ገልፀዋል።

የወገን ኃይልን መቋቋም የተሳነው ጠላት እየዘረፈና እያወደመ እንዳይሄድ በየአካባቢው ያለው ህዝብ ተደራጅቶ አካባቢውን በመጠበቅ፣ መረጃ በመስጠት፣ ሰራዊቱን በደጀንነት ማገዝ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ኀብረተሰቡ ይህን በማድረግ ህዝብና አገርን የማዳን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

በአማራ ክልል ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በ3 ቀናት 265 ሺህ በላይ ኩንታል ምግብ ነክ እርዳታ መቅረቡን አንስተው፤ በአፋር ክልልም 76 ሺህ ተፈናቃዮች ከ36 ሺህ ኩንታል በላይ መሰረታዊ ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ድጋፉን ያደረጉት መንግሥትና አጋር አካላት በመቀናጀት መሆኑንም ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል በአየር የሚቀርበው ሰብዓዊ ድጋፍ መቀጠሉንና 83 የድጋፍ ቁሳቁስ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በሰመራ በኩል ወደ ክልሉ መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም