በዞኑ የአሸባሪው ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

78

ፍቼ ህዳር 17/2ዐ14/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተደረገ ሰላም ማስከበር ዘመቻ የአሸባሪው ሸኔ አባላት ከነትጥቃቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

በዞኑ የዕዝ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አብርሃም ጋዲሣ እንደገለፁት የአሸባሪው ሸኔ አባላት ከነትጥቃቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፉት አስር ቀናት የፀጥታ ሀይሎች ተቀናጅተው ባደረጉት የፀጥታ ማስከበር ዘመቻ ነው፡፡

የሽብር ቡድኖቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ክላንሽኮቭ ጠብ መንጃዎች፣ የእጅ ቦምቦች፣ ሽጉጦች፣ የቡድን መሳሪያዎችና ጥይቶች መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡

የፀጥታ አካላቱ በተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤቶች ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት በርካታ የፀጥታ አስከባሪዎች አልባሳት፣ ሀሰተኛ ነዋሪዎች መታወቂያና ሰነዶች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በርካታ ፀጉረ ልውጥ ሰዎችና የአሸባሪው ሸኔ መረጃ አቀባባዮች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

አሸባሪዎቹን ህወህትና ሸኔ በመደምሰስ የሕልውና ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ከሕዝብ ጋር ሆኖ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም አሸባሪው ሸኔ ሲንቀሳቀስባቸው በነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማትና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የአገልግሎት መስጫዎች ስራ እንዲጀምሩ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን ሆነ ባደረገው ትግል የሽብር ቡድኑን አባላት በመደምሰስ የሸኔ እኩይ ዓላማ እንዲመክን ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

አሁንም ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ፣ ሰርጐ ገቦችን በማጋለጥና የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ባለማስተጋባት የህልውና ዘመቻውን እንዲያግዝ አሳስበዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ዳግም የአካባቢው ስጋት እንዳይሆን ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎችና ነጋዴዎች ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን እያደረጉት ያለውን ትግል አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

በፀጥታ ማስከበር ተሳትፎ በማድረግ ላይ ያሉት የሀገር ሽማግሌ አቶ ዳመና አበራ "አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞ ሕዝብ ግንባር ቀደም ጥያቄ ሰላምና ፀጥታ መሆኑን ያልተረዳ ነው" ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ የህወሓት ተላላኪ በመሆን የኦሮሞ ሕዝብ በማያውቀውና በማይፈልገው የሴራ ፖለቲካ በመተብተብ ኦሮሞን ማወክ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ወጣቶች ማህበር አባል ወጣት ዳኜ ደርቤ "ሸኔ የኦሮሞ ሕዝብ ሰላምና ፀጥታ በመንሳት የጥቂት ግለሰቦችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ  ፍላጐት ማርካት  መሆኑን መገንዘብ ይገባል" ብለዋል፡፡

ይህንንም አጥብቆ ለመካላከል ወጣቶች የክተት ጥሪን አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የህልውና ትግሉን እንዲቀላቀሉ አሳስባል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም