የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በአገር ህልውና ማስከበር ዘመቻው ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊት አባላት የምሳ ግብዣ አደረጉ

236

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2014 (ኢዜአ) የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በአገር ህልውና ማስከበር ዘመቻው ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊት አባላት የምሳ ግብዣ አደረጉ።

“የቅድሚያ ለእናት አገር ኢትዮጵያ” የኮሚቴ ሰብሳቢ አርቲስት የሽዋጌጥ ጫኔ፤ በቤላ ማገገሚያ ማዕከል የተደረገው የምሳ ግብዣ በጀግንነት ለአገራቸው ዋጋ ለከፈሉ የሰራዊት አባላት መሆኑን ገልጿል።

የጀግናው ሰራዊት አባላት “እናት አገሬ” ብለው አሸባሪውን በጀግንነት በማፋለም ለአገራቸው ቁርጠኛ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩ ናቸው ብሏል።

ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም የገጠማትን ፈተና በድል ለመወጣት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እያደረጉት ያለው ተጋድሎ ታሪክ የማይዘነጋው ጀግንነት መሆኑን የገለጸው አርቲስት የሽዋጌጥ ሁላችንም ለአገራችን ህልውና ማስጠበቅ ተዘጋጅተናል ነው ያለው።

የቤላ ማገገሚያ ማዕከል አስተባባሪ ኮሎኔል አባተ ምስጋናው፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ትብብርና መረዳዳትን የምትሻበት ወቅት በመሆኑ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመታቸው ዜጎችን ከዳር ዳር ይበልጥ ያነሳሳ እና ለድጋፍ ያዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል።