ሠራተኞቹ የሚኒሻ አበላትን የደረሰ ሰብል ሰበሰቡ

78

ባህር ዳር ህዳር 17/2014  (ኢዜአ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሠራተኞች ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት በግንባር የተሰለፉ የሚኒሻ አበላትን የደረሰ ሰብል ሰበሰቡ።
የሁለቱ ተቋማት ሠራተኞቹ ዛሬ በጋራ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል የሰበሰቡት በባህር ዳር ከተማ ዙሪያ ወረዳ ይባብ ቀበሌ ነው።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባልደረባ አቶ ደሳለኝ ቢራራ ለኢዜአ እንደገለጹት ወራሪውን ህወሓት ለመደምሰስ ህብረተሰቡ ወደ ግንባር በመዝመት ጭምር መከላከያን እያገዘ ነው።

"እኛም ሀገርና ህዝብ ለማዳን ቤተሰቦቻቸውን ጥለው በግንባር ደምና አጥንታቸውን እያፈሰሱና እየከሰከሱ ያሉ ሚሊሻዎች “ሰብላቸው ሳይሰበሰብ እንዲቀር አንፈቅድም” በሚል ተነሳስተን ሰብላቸውን እየሰበሰብን እንገኛለን” ብለዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሠራተኛ ወይዘሮ ጥሩአንቺ የሰራ በበኩላቸው "እኛን ለማኖርና ሀገራቸውን ለመታደግ በግንባር እየተዋደቁ የሚገኙ ዘማች ቤተሰቦችን ሰብል መሰብሰብ ግዴታችን ነው" ብለዋል።

የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ከመሰብሰብ ባለፈ በግንባር ተሰልፈው አሸባሪውን ህወሓት ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

"የዘማች ቤተሰቦች ሰብል ሳይሰበሰብ አይቀርም" ያሉት ወይዘሮ ጥሩአንቺ፣ እኛም ከጎናቸው መሆናችንን ለማሳየት ሰብላቸውን በመሰብሰባችን ደስተኛ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

ባለቤታቸው ጠላትን ለመፋለም ወደግንባር በመሄዱ ኩራት እንደሚሰማቸው የተናገሩት ደግሞ የይባብ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እህትነሽ ምናለ ናቸው።

"የደረሰው ሰብል ሳይሰበሰብ ሊቀር ነው ብዬ ሰግቼ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ድንገት ሳላስበው የደረሰ የበቆሎ ሰብሌ በመሰብሰቡ ከልብ ተደስቻለሁ" ብለዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አስቻለው አየሁዓለም በበኩላቸው ተቋሙ ለህብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃ ከማድረስ ባለፈ ሠራተኛውም የወር ደመወዙን በመስጠትና በግንባር ዘምቶ ጠላትን በመፋለም የህልውና ዘመቻውን እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

"ዛሬ ደግሞ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ ከጎናቸው መሆናችንን አረጋግጠናል" ብለዋል።

ወደ ግንባር የዘመቱ የፀጥታ አካላትን ሰብል መሰብሰብም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን መንከባከብ የሁላችንም ግዴታ መሆን ይኖርበታል ሲሉም አክለዋል።

"የህልውና ዘመቻውን ለማገዝ ከስንቅ ዝግጅት በተጨማሪ የዘማች ቤተሰቦችን የደረሰ ሰብል መሰብሰብ የሁላችንም ግዴታ ነው''  ያሉት ደግሞ የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ህሊና መብራቱ ናቸው።

ዛሬ የተጀመረው የሰብል መሰብሰብ ሥራ በቀጣይም ራቅ ወዳሉ የገጠር አካባቢዎች በየሳምንቱ በመሄድ  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ሀገራቸውን ከአሸባሪና ወራሪ ጠላት ለመታደግ በግንባር እየተፋለሙ የሚገኙ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሌላውም ህብረተሰብ ድጋፍና እገዛውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም