ለሀገር ህልውና መረጋገጥ ግንባር የሚገኙትን መሪያችንን አርአያነት እንከተላለን

62

ድሬዳዋ ፤ኅዳር 17/2014(ኢዜአ) ለሀገር ህልውና መረጋገጥ ግንባር የሚገኙትን መሪያችንን አርአያነት እንከተላለን የሚሉት የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮችና የአስተዳደሩ የቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሴት ሠራተኞች ናቸው።

ሀገራዊ ጥሪውን ተከትለውም  ሰራተኞቹ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ ማዘጋጀት የጀመሩ ሲሆን ይህንኑ የስራ እንቅስቃሴ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃርና ሌሎች አመራሮች ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለአገር ህልውና መረጋገጥና አፍሪካን ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለማላቀቅ አርአያ ሆነው ግንባር መዝመታቸው በአፍሪካዊያንና በጥቁር ሕዝቦች ጭምር መነቃቃት እንደፈጠረ ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

''እሳቸው ግንባር ሆነው ቤት የሚውል  ሰው አይኖርም፤ ግንባር የምንዘምተው እንጓዛለን፤ የቀረነው ደግሞ በልማትና በተሰማራንበት መስክ የተሻለ ውጤት እናስመዘግባለን፤አካባቢያችንን እንጠብቃለን'' ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ የነዋሪዎች ተነሳሽነት መጨመሩን ይናገራሉ።

የእንዝመትን ጥያቄዎችና የስንቅ ዝግጅትን ለአብነት በመጥቀስ።

አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት አሸባሪውን ህወሃት ለማትረፍ፣ የአፍሪካ የነጻነት ፋናና የአፍሪካ ኩራት የሆነችውን ኢትዮጵያ ለማፍረስ የሚያደርጉት ጥረት በመገንዘቡ ሀገሩን ለማዳን እየተረባረበ ነው ብለዋል፡፡

''የትኛውም የድሬዳዋ አመራር ግንባር ዘምቶ ኢትዮጵያን አድኖ ደማቅ ታሪክ ውስጥ ለመጻፍ ተዘጋጅተናል'' ሲሉም ኃላፊው የአመራሩን ቁርጠኝነት አስታውቀዋል፡፡  

የአስተዳደሩ ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው፤ የቢሮው ሴት ሠራተኞች ሀገራዊ ጥሪውን በመቀበል ለሠራዊቱ  ደምና ገንዘብ በመለገስ እንዲሁም ስንቅ በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የቢሮው  ሠራተኛ ወይዘሮ ቤተልሄም ታፈሰ ''የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል ለጀግና ሠራዊታችን ደረቅ ስንቅ እያዘጋጀን ነው'' ብለዋል፡፡

''ለሠራዊቱ ስንቅ ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ግንባር ድረስ ዘምተን በዕውቀታችንና በጉልበታችንን ሀገርን ለማዳን ተዘጋጅተናል'' ያሉት ደግሞ ሌላዋ የቢሮው ሠራተኛ ወይዘሮ አልማዝ ተፈራ ናቸው፡፡

ወይዘሮ ኑሪያ ዓሊ በበኩላቸው ''ለሀገር ህልውናና ነፃነት ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ቆርጦ ጦር ሜዳ የሚውል መሪ በማግኘታችን ከፍተኛ ወኔና መነቃቃት ፈጥሮብናል'' ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጥሪ ተከትለን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ ከማዘጋጀት ባሻገር ወደ ግንባር እንዘምታለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም