ጥምረቱ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል - ጤና ሚኒስቴር

74

አዳማ ፤ ህዳር 17/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት በድንገተኛና ፅኑ ህሙማን ክፍሎች ጥራቱን የጠበቀ ህክምና አገልግሎት ለመስጠት እንዳስቻለ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በሶስተኛ የትግበራ ምዕራፍ የሆስፒታሎች ጥምረት በእናቶችና ህፃናት ሞት ቅነሳ፣ በድንገተኛና ፅኑ ህሙማን ክፍሎች የታዩት ለውጦችና የአራተኛ ዙር ቀጣይ ትኩረት  ላይ ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል።

በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ህሊና ታደሰ  እንደገለጹት፤ ሆስፒታሎች በፈጠሩት ጥምረት የሰውና ሌሎች ሀብቶች በመጋራትና በመደጋገፍ ውጤታማ ሆነዋል ።

በሶስት የትግበራ ምዕራፎች በተለይ በእናቶችና ህፃናት ሞት ቅነሳ፣ የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥና የጤና ሴክተርን ከማሻሻል አንፃር ጥሩ ተሞክሮዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም በመነሳት "ኢንፌክሽኖችን" ከመከላከል፣ በድንገተኛና ፅኑ ህሙማን በተለይ በድንገተኛ የሆስፒታሎች የህክምና ክፍል ውስጥ የአገልግሎት ጥራት መሻሻሉን ዶክተር ህሊና አስረድተዋል።

የምክክሩ መድረክ ዓላማ ባለፉት ምዕራፎች የተገኙትን መልካም ተሞክሮዎች ለማጠናከርና አራተኛውን ምዕራፍ የጥምረቱ አባል በሆኑ አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ሪፈራል ሆስፒታሎች ለማስጀመር እንዲቻል ለማመቻቸት ነው ብለዋል።

በአራተኛው ምዕራፍ የተመረጠው አቅጣጫ የህክምና የአገልግሎት ጥራትን በሁሉም የህክምና ክፍሎች ከማሻሻል ባለፈ በመረጃ ላይ የተመሰረተ አገልግሎት መስጠት እንደሆነ አብራርተዋል።

በዚህም ሆስፒታሎች የሚሰጡት የህክምናና የጤና አገልግሎት የጥናትና ምርምር ግኝቶች ላይ እንደሚመሰረት አመልክተዋል።

የህሙማንና የተገልጋዮችን ፍላጎት ብቻ መሠረት በማድረግ የባለሙያዎችን ልምድና ዕውቀት በተጨባጭ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል።

በጥምረቱ ትግበራ ልዩ ትኩረት በዋናነት የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የፅኑ ህሙማን፣ የቀዶ ጥገና አገልግሎት፣ የጨቅላ ህፃናት ህክምና፣ የህፃናት ሞት ቅነሳና የተመላላሽ ህክምና አገልግሎት ማሻሻል መሆናቸውን  ዶክተር ህሊና አመላክተዋል።

ለስራውም ውጤታማነት ከሆስፒታሎች ጥምረት አመራሮች በተጨማሪ ሚኒስቴሩና የክልል ጤና ቢሮዎች ትኩረት እንዲሰጡት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በአፋርና በአማራ ክልሎች ከ2ሺህ በላይ የጤና ተቋማት በመዝረፉና በማውደሙ  በአራተኛው ዙር የሆስፒታሎች ጥምረት ትግበራ ተፈናቃዮችን በተለየ ትኩረት በአገልግሉቱ ተደራሽ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

የአራተኛው ዙር የሆስፒታሎች ጥምረት ትግበራ ፕሮግራም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የጤና አገልግሎት ለማስፋትና ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ያሉት ደግሞ በሚኒስቴሩ የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር አባስ ሐሰን ናቸው።

ፕሮግራሙ በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታካሚዎችን የኋላ ታሪክ በሶፍት ዌር መዝግቦ በማስቀመጥና  ከሆስፒታል-ሆስፒታል የተገልጋዮች ትክክለኛ መረጃ በማኖር የመረጃ ችግር እንዳይፈጠር የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም