ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሶች ከነተጠርጣሪዎች ጋር ተያዙ

90

ሐረር ፤ ህዳር 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሶች ከነተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስራ መዋላቸውን የክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ አስታወቀ።
የኮሚቴው አባልና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር  ነስሪ ዘከርያ ዛሬ እንደገለጹት፤  በክልሉ የአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ እኩይ ተግባርን ለመቆጣጠር የዕዙ የጸጥታ ኮሜቴ   ተዋቅሮ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በዚህም  በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤቶች በተደረገው ብርበራ   ለሽብር  ተግባር ሊውሉ የነበሩ በርካታ  የጦር መሳሪያዎች፣የጸጥታ አካላት  አልባሳትእና ሌሎች  ቁሳቁሶች መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል።

ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ  ፣ ሽጉጦች፣በግለሰብ እጅ መቀመጥ የሌለበት የጦር ሜዳ መነጽሮች እና ቴሌስኮፖች  በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ይገኙበታል።

እንዲሁም  በርካታ የተለያዩ ሰነዶች ፣የሞባይል ስልክ ሲም ካርዶች፣ላብቶፖች፣ሞባይሎች እና ሌሎች ቁሶች መገኘታቸውን አመልክተዋል።

ይህ ጉዳይ የተፈጸመው ከአሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔ ጋር ግንኙነት ባላቸው ተጠርጣሪ ግለሰቦች በመሆኑ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ  ነው ኮሚሽነር ነስሪ ያመለከቱት።

ለአሸባሪዎቹ የፋይናንስ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ከባድ ተሽከርካሪዎችና ብዛት ያላቸው የባንክ  ሂሰብ ደብተሮች  እንዲታገዱ መደረጉን ገልጸዋል።

የክልሉ ነዋሪ ከጸጥታ አካላት ጋር  በመሆን እያከናወነ የሚገኘውን የአካባቢ ጥበቃ እና የደጀንነት ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም