የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አመራሮች ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ

69

ህዳር 17/2014 (ኢዜአ)  የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አመራሮች እንዲሁም በስሩ የሚገኙ የጽህፈት ቤት ሃላፊዎች ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ፡፡
የአገር ህልውና ማስከበር ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ ሁሉም ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚያደርገውን ደጀንነት ሚና አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመራሮቹ ተናግረዋል።

ከደም ለጋሾቹ መካከል በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሒክማ ኽይረዲን፤ ህዝቡ በድጋፍም በደጀንነትም ለአገሩ ቆሟል ብለዋል።

የፐብሊክ ሰርቪሱ አመራር “ደሜን ለአገሬ” በሚል ደሙን መለገሱን ገልጸው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት የፐብሊክ ሰርቪስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሽብር ጥላሁን፤ ለመከላከያ ሰራዊት ደም መለገስ ትንሹ ስጦታ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በአሁኑ ሰዓት ደም በመስጠት ህይወት ማትረፍ በመሆኑ ሁላችንም ልንሳተፍበት ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ ያሬድ ለገሰ፤ ለህልውና ዘመቻው ሁሉም በሚችለው እና በያለበት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።