የምዕራብ ሐረርጌ ዞን አመራሮች የሕልውና ዘመቻውን ይቀላቀላሉ

66

ጭሮ፣ ህዳር 17/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በየደረጃው ያሉ አመራሮች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን የጀግንነት ተጋድሎ አርዓያነት ተከትለው የህልውና ዘመቻውን እንደሚቀላቀሉ አረጋገጡ።

የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶፊቅ አህመድ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ "እኔ በሕይወት እያለሁ ኢትዮጵያ አትፈርስም" ያሉትን ቃል ለመጠበቅ የሕልውናው ዘመቻ አካል ሆነዋል።   

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕልውና ዘመቻውን በግንባር ሆነወ መምራታቸው በሀገራቸው የማይደራደሩ ቆራጥ መሪ ስለመሆናቸው ከማሳየት ባለፈ ሕዝቡ ለድጋፉ ይበልጥ እንዲነሳሳ ማድረጉን  ተናግረዋል።

ዶክተር ዐቢይ ወደስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ዛሬ የተናገሩትን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በተጨባጭ ያሳዩ መሪ ናቸው ብለዋል።

እሳቸውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን አርዓያ ተከትለው ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

"አሸባሪው ህወሓት ለ27 ዓመታት ህዝብና ሀገር  የበደለው ሳያንሰው አሁንም በዜጎች ላይ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት ተግባር መፈጸሙ ኢትዮጵያ ጠል መሆኑን በተጨባጭ ያሳያል" ብለዋል

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በየ ደረጃው የሚገኙ አመራሮች የዶክተር ዐብይን ፈለግ ተከትለው በግንባር አሸባሪው ህወሓትን ለመፋለም ተዘጋጅተዋል።

ወደግንባር የመዝመት እርምጃ  ከራሳቸው እንደሚጀምሩ ገልጸው፣ በሽብር ቡድኑ የተደቀነውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ መቀልበስ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።  

በተለይ ሀገር ለመበታተን ቆርጦ የተነሳውን አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ ከኋላ ደጀንነት ባለፈ በግንባር ተሰልፈው የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

"ሁሌም ከመንግስታችን ጎን እንቆማለን፣ የሀገርና የህዝብ ደህንነትን ለማስጠበቅ ሁላችንም በአንድነት እንዝመት" ብለዋል አቶ ቶፊቅ።

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድ ኡመር በበኩላቸው ሀገር አሁን ለገባችበት የሕልውና ዘመቻ የከተማ አስተዳደሩና ነዋሪዎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል።

በዚህም የከተማዋ ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ተጨማሪ አቅም መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ  ትግሉን በግንባር መምራታቸው እሳቸውም ለመዝመት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝብና ሀገርን የሚያኮራ ተግባር እየሰሩ ነው" ያሉት ከንቲባው፣ "ሕዝብና መሪው እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ድምፅ ተናጋሪ መሆናቸው ሊጠናከር ይገባል" ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ የጥፋት ተግባር ለመታደግ ሁሉም በየደረጃው ከቁሳቁስ ድጋፍ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መነሳት እንዳለበትም  አስገንዝበዋል።

"ለእናት ሀገር ጥሪ ከማንም በላይ መድረስ ያለብን እኛ ልጆቿ ነን" ያሉት ከንቲባው፣ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመለላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ኢትዮጵያን እንደሚታደጉ አረጋግጠዋል።  

ብልጽግና ፓርቲ የጭሮ ከተማ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ  ከማል   በበኩላቸው "   በእኛ ዘመን ጦር ለመምራት ወደ ግንባር ከዘመቱ መሪዎች ዶክተር ዐቢይ የመጀመሪያው ናቸው" ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሕዝብና ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በመቆም ትግሉን እንደሚቀላቀሉ የገለጹት አቶ መሀመድ ፣ ለሀገርና ለህዝብ መሞት ከምንም በላይ ትልቅ ክብር መሆኑም ተናግረዋል።

በሕልውና ዘመቻው ኢትዮጵያ አሸንፋ እንድትወጣ ሁሉም የመንግሥትን ጥሪ ተቀብሎ ዘመቻውን እንዲቀላቀልና የጥፋት ቡድኖችን እንዲደመስስ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ መሀመድ "ለሀገር ከመሞት በላይ ክብር የለምና ራሴና የምመራቸውን አመራሮች ይዤ የትግሉን ሜዳ እቀላቀላለሁ" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሀገር ለማዳን በጦር ሜዳ ሲሰለፉ የማይዘምቱበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አቶ መሀመድ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም