የአፍሪካ ኀብረት፤ ለአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል ማዕከል ግንባታ የቻይና መንግሥት ላደረገው ድጋፍ አመሰገነ

88

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን በአዲስ አበባ እየተገነባ ላለው የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል ማዕከል ግንባታ የቻይና መንግሥት ላደረገው ድጋፍ አመሰገነ። የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል ማዕከል ግንባታ አሁን ላይ 45 በመቶ መድረሱም ተገልጿል።
የማዕከሉን የግንባታ ሂደት ከአፍሪካ ህብረት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከቻይና ኤምባሲ የተውጣጣ ልኡክ ጎብኝቶታል።  

የማዕከሉ ግንባታ የመጨረሻ ወለል ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ከዚሁ ጎን ለጎን ተካሂዷል።

የማዕከሉ ግንባታ ሙሉ ወጪ በቻይና መንግሥት የተሸፈነ ሲሆን በአፍሪካና በቻይና መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ነው የገለጸው።

በአፍሪካ በተለይም ተላላፊ በሽታዎች የሚያመጡት ተጽዕኖ እየበረታ በመምጣቱ የማዕከሉ እውን መሆኑ በሽታን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን እንደሚያጠናክር ተመላክቷል።

የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ተወካይ አሚራ ፋድል መሃመድ የማዕከሉን ግንባታ ለማስጀመር እንደአውሮፓዊያን አቆጣጠር ነሃሴ 2020 ስምምነት መፈረሙን አስታውሰው በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታው እዚህ መድረሱ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በ348 ቀናት ውስጥ የማዕከሉ ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ መጠናቀቁ ትልቅ የቁርጠኝነት ማሳያ ነው ያሉት ተወካይዋ ለዚህም የቻይና መንግሥት ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

የማዕከሉ መገንባት በቻይና እና አፍሪካ መካከል በኢኮኖሚ፣ በጤናና በሌሎችም ማህበራዊ ዘርፎች ያለው ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።     

በአፍሪካ ኀብረት የቻይና ሚሺን ኃላፊ አምባሳደር ሊዩ ዩዥ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ ጫና እያሳረፈ ቢሆንም የአፍሪካንና የቻይናን ግንኙነት አላቆመውም ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያደርጉትን ጥረት ቻይና በቁርጠኝነት እንደምትደግፍ አረጋግጠው የማዕከሉ ግንባታ ለዚህ ተግባራዊ ምሳሌ መሆኑን አክለዋል።

የአፍሪካ ኀብረት ከያዛቸው ውጥኖች አንዱ አጀንዳ 2063 እንዲሳካ የቻይና መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።  

ቻይና እና አፍሪካ በጋራ ብሩህ ጊዜ እንዲኖራቸው በጋራ መስራታችን የበለጠ ይጠናከራልም ነው ያሉት።