የአሁኑ ጦርነት ዶክተር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የተዘራ ዘር ውጤት ነው- ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ

143

አሁን በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ጦርነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የተዘራ መጥፎ ዘር ውጤት መሆኑን የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ Truth is a major casualty of the war in Northern Ethiopia በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሁፍ ላይ እንዳመለከቱት ጦርነቱ ካሳየን አሉታዊ ውጤቶች መካከል አንዱ እውነት እንድትደበቅ ማድረጉ ነው ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን አሁናዊ ጉዳይ ከአፍጋኒስታን ጋር እያነጻጸሩ ማቅረባቸው ሁለቱ ሀገራት የየራሳቸው ታሪካዊ ዳራ ያላቸው በመሆኑ በፍጹም ለንጽጽር የሚቀርቡ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡

እውነታውን በመካድ ኢትዮጵያን ከፈረሱ ሃገራት ጋር ለማነጻጸር መሞከር ስህተት ነው ብለዋል።

ተመራማሪው አክለውም ካቡል የፈረሰችበት ዋና ምክንያት የአሜሪካ ጦር ጣልቃ በመግባቱ እና ፍላጎቱን ካሳካ በኋላ ጥሎ መውጣቱ ነው የሚሉት ተመራማሪው ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት የውጭ ጦር በሌለበት እንዴት ለንጽጽር ይቀርባሉ ሲሉም ይሞግታሉ፡፡

ታሊባን ወደ ካቡል እየገፋ በሚመጣበት ጊዜ ከአፍጋኒስታናውያን ምንም አይነት የመከላከል እርምጃ እንዳልገጠመው የጠቀሱት ፕሮፌሰር ባህሩ አሁንም ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር መላ ህዝቡ ልክ በሶማሊያ እና በኤርትራ ወረራ ጊዜ የነበረው አይነት ህዝባዊ ንቅናቄ በማድረግ ከመንግስት ጎን መቆም ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑን የሽብር እንቅስቃሴ ታሪካዊ ዳራ ባሳዩበት በዚህ ጽሁፋቸው ላይ ቡድኑ በመላ ኢትዮጵያውያን በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በደብቡ ክልሎች በተቀሰቀሱ ህዝባዊ እምቢተኝነት ከስልጣን መወገዱን አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ጦርነት የገጠመችው ከ27 ዓመታት በላይ ፖለቲካውንም ኢኮኖሚውንም በህብረ-ብሔራዊነት ስም ተደራጅተው የነበሩ ድርጅቶችን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ ከነበረ የሽብር ቡድን ጋር ነው ብለዋል፡፡

ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ተከትሎ በአዲስ መልክ የተደራጀው መንግስት የሽብር ቡድኑ ዳግም ስልጣን ላይ ያለው የበላይነት እንዳያገኝ ለማድረግ በመናበብ በተሰራ ስራ የሽብር ቡድኑ ዳግም ስልጣን የመጠቅለል ድብቅ ዓላማ በማክሸፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መምረጡን አስታውሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ያለ ቅድመ-ሁኔታ በሽብርተኝነት ተፈርጀው ወደ ሀገር እንዳይገቡ ተከልክለው የነበሩት እንደ ኦነግ እና ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች ሀገራቸው ገብተው በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ፣ የምርጫ ቦርድ እና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነጻነታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ በአዲስ መልክ እንዲደራጁ እንዲሁም በርካታ የህግ ማሻሻያዎች ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

አሁን ከሽብር ቡድኑ ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ለበርካታ ዓመታት የብሔር ልዩነት ላይ ተጣብቆ የቆየውን ፖለቲካዊ ትርክት ሊቀይር የሚችል ንግግር ካደረጉበት ወቅት ጀምሮ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓን ኢትዮጵያኒዝም አቀንቃኝነት ደግሞ የሽብር ቡድኑ ቀደም ሲል ሲያቀነቅን ከነበረው የብሔር ተኮር ኢትዮጵያ ጠል ትርክት ጋር የሚቃረን በመሆኑ የሽብር ቡድኑ አመራሮች መቀሌ በመክተም ጦር ማደራጀት እንዲጀምሩ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

በፌዴራል መንግስት እና በሽብር ቡድኑ መካከል የተፈጠሩ ቅራኔዎች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ መንግስት በራሱ ካደረገው ጥረት በተጨማሪ በርካታ አካላት ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢያደርጉም በቡድኑ እምቢተኝነት ውጤታማ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የሽብር ቡድኑ በነጻ ሀገር ውስጥ ሌላ ነጻ ሀገር የመሰረተ በሚመስል መልኩ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ሀገራት ምርጫዎቻቸውን ባራዘሙበት ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሀገራዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ጊዜ ቢያራዝምም ቡድኑ ክልላዊ ምርጫ በራሱ ማከናወኑን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ በክልሉ ለበርካታ ዓመታት ህዝቡን ሲያገለግሉ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ መብረቃዊ እርምጃ በመውሰድ በጅምላ መጨፍጨፉን በራሱ አመራሮች አንደበት ገልጾታል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን በጦርነት ውስጥ በተቀናቃኝ ሀይሎች ለችግር የሚጋለጥ ህዝብ እንደሚኖር ግልጽ ቢሆንም ፕሮፌሰር ባህሩ የፌዴራል መንግስት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ፍላጎት ያለው መሆኑን የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ በመወሰን አሳይቷል ብለዋል፡፡

መንግስት ሰራዊቱን ከክልሉ በማውጣት ጭምር ለሰላማዊ መፍትሔ ያለውን ቁርጠኝነት ቢያሳይም የሽብር ቡደኑ ይህን ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደ ሰላማዊ ድርድር ከመምጣት ይልቅ በአዲስ መልክ የማጥቃት አድማሱን በአማራ እና አፋር ክልሎች የወረራ እና የጥቃት  እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡

በዓለም አቀፍ መገናኛ ዘዴዎች እና የሚወጡ ትንታኔዎች በአጠቃላይ ጉዳይ ላይ ማተኮር ሲገባቸው ጦርነቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በሽብር ቡድኑ መካከል እንደሚካሄድ አድርገው ሽፋን መስጠታቸውን ለማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ብቻ በማተኮር እኤአ በ2019 የተሸለሙትን የኖቤል ሽልማት እንደ ዋና ማጥቂያ መሳሪያነት በመጠቀም እንዲሁም ህዝባዊ ቅቡልነት እንደሌላቸው አድርጎ በመሳል የተሳሳተ ዘገባ እያሰራጩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም