ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕልውናውን ጦርነት በግንባር መምራታቸው ለምዕራባዊያንም መልዕክት አለው

166

ደብረ ማርቆስ ህዳር 17/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሀገር ሕልውና እና ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከአሸባሪው ህወሓት ጋር እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በግንባር መምራታቸው ለምዕራባዊያን ጭምር ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ መሆኑን የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሀገር ሕልውናን ለማስከበር ከአሸባሪው ህወሓት ጋር እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በግንባር መምራታቸው ለምዕራባዊያን ጭምር የአትንኩን ባይነትን መልዕክት ያስተላለፈ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሽብር ቡድኑን ግብዓተ መሬት በአጠረ ጊዜ ለመፈጸም በጀግንነት እየተፋለመ ያለውን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በግንባር መምራታቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ለቋመጡ ምዕራባዊያን ትልቅ መልዕክት አለው።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የጠቅላይ ሚኒስትሩ “እናሸንፋለን፤ አትጠራጠሩ” እምነትና ወኔ ሌሎችን የሚያስደንቅ፣ የሚያደፋፍርና የሚያጀግን መሆኑን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል ተጠሪና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ገናነው ጀንበሩ እንዳሉት ህወሓት በሕዝብ ትግል ከስልጣኑ ተወግዶ ወደ መቀሌ ከመሸገ በኋላ ከሀዲነቱን በግልፅ አሳይቷል።  

በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ከጀርባ ጥቃት ከመፈጸም ጀምሮ በተለይ በአማራና አፋር ክልሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ፈጽሟል፤የሀገር ሀብት አውድሟል።

በመንግሥት በኩል የሽብር ቡድኑን ባለበት በመደምሰስና አቅመ ቢስ በማድረግ በኩል በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ምሁሩ ጠቅሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሕልውና ጦርነቱን በግንባር ለመምራት  መዝመታቸው በጣም አስፈላጊና በኢትዮጵያዊያን ላይ እየታየ ያለውን ሀገራዊ ስሜት ይበልጥ የሚያጎለብት ነው።

“ዶክተር ዐቢይ የአባቶቻቸውን ታሪክ የደገሙ፣ ዳግመኛ ዓድዋን የተገበሩ ጀግና መሪ ናቸው”  ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰሩ ገናነው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተጋድሎ አድንቀዋል።

“የእሳቸው መዝመት ለሀገር ውስጥ ባንዳ ብቻ ሳይሆን በእጅ አዙር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ለቋመጡት ምዕራባዊያን ጭምር አትንኩን ባይነትን መልዕክት ያስተላልፋል” ብለዋል።

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ግንባር እንገናኝ’ ጥሪ በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንዲሆንም ከየአቅጣጫው ኢትዮጵያዊያን ከጎናቸው መቆማችንን ማጠናከር አለብን” ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የሶሻል ሳይንስና ሂውማኒቲ ኮሌጅ ዲን ዶክተር አማረ ሰውነት እንዳሉት በዓድዋ ዘመቻ ዓፄ ምኒልክ በክተት ጥሪ ህዝባቸውን አሰልፈው በመሄዱባቸው ለጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን አስረከበውናል።

“አሁንም ዶክተር ዐቢይም ቀደምት ሀገር ወዳድና ጀግና የኢትዮጵያ መሪዎች ያስረከቧቸውን ወኔ እና ታሪክ ይዘው ወደ ግንባር መዝመታቸው ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ ነፃነት ፈላጊ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንን የሚያነሳሳ እና የሚያኮራ የአልደፈር ባይነት ታሪካችንን ያስቀጥላል” ብለዋል።

በሠራዊቱ ላይም ሆነ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የሞራል ግንባታ የሚፈጥርና በአጠረ ጊዜ ጦርነቱን  ለማጠናቀቅ የሚያስችል መሆኑንም ዶክተር አማረ አስረድተዋል።

”ሀገር እና የሚመራውን ህዝብ የሚወድ መሪ እንደ ተራ ግለሰብ ሀገሩን ለቆ አይሄድም”ያሉት ዶክተር አማረ፣ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝብና ሀገር ወዳድ መሆናቸውን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሕዝባቸው ጋር ግንባር ዘምተው አረጋግጠዋል” ብለዋል።

ከየአቅጣጫው የተጋረጠብን አደጋ በርካታ ቢሆንም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ለሕዝባቸው የሚንጸባረቀው የ”እናሸነፈለን፤ አትጠራጠሩ” ፅኑ እምነትና ወኔ የሚያስደንቅ፣ ሌሎችንም የሚያደፋፍርና የሚያጀግን መሆኑን ተናግረዋል።

“በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትራችን ሀገርና ህዝብ የማዳን ዘመቻ እንዲሳካና በሀገር ላይ የተደቀነው አደጋ እንዲቀለበስ እኛም ፈጥነን ከጎናቸው መሰለፍ ይኖርብናል” ሲሉ ዶክተር አማረ አክለዋል።

ምሁራኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደግንባር መዝመት የዓድዋንና ቀደምት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሆኑ መሪዎቿን ታሪክ የደገመ መሆኑንም ተናግረዋል።