ተቋማዊ ማሻሻያው ድንገተኛ ውሳኔ ሳይሆን በሀገሪቱ የተካሄደው ዘርፈ ብዙ የተሃድሶ ሂደት አካል ነው

349

ህዳር 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) “በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተደረገው ተቋማዊ ማሻሻያ ድንገተኛ ውሳኔ ሳይሆን በሀገሪቱ የተካሄደው ዘርፈ ብዙ የተሃድሶ ሂደት አካል ነው” ሲሉ አምባሳደር ሬዲዋን ሁሴን ገለጹ።

ዓመታዊው የአምባሳደሮችና ሚሲዮን መሪዎች ስብሰባ “ዲፕሎማሲያችንን በአዲስ ምዕራፍ ለላቀ ለውጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በስብሰባው ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ሬዲዋን ሁሴን በሚኒስቴሩ የተሃድሶ ሂደት ክፍተቶችን በመለየት እና ተቋሙን ለመለወጥ እቅድ በማውጣት ሂደት ላይ በዝርዝር ገለጻ አድርገዋል።ሚኒስትር ዴኤታው የተደረገው ተቋማዊ ማሻሻያ ድንገተኛ ውሳኔ ሳይሆን በሀገሪቱ የተካሄደው ዘርፈ ብዙ የተሃድሶ ሂደት አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም እየተካሄደ ያለው የተቋማዊ ማሻሻያ ሂደት የቴክኖሎጂ ሽግግርችን እና የጂኦስትራቴጂካዊ ጥቅሞችና ለውጦችን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን ተናግርዋል፡፡

አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ በኢትዮጵያ የሚፈጥሯቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት እና ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ትብብር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አምባሳደር ሬዲዋን እየተካሄደ ባለው ስብሰባ መሪ ቃል መሰረት በዲፕሎማሲያዊ አሰራር ሂደት ወቅታዊ ፈተናዎችን በመገንዘብ እና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በማሸጋገር ረገድ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በዚህ ለሶስት ቀናት በሚቆየው ውይይትም የ2013በጀት አመት የስራ አፈጻጸምን በመገምገም በተቋማዊ ማሻሻያ እና በ2014 በጀት አመት እቅድ ላይ እንደሚወያዩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡