በኢሉባቦር ዞን የመንግስት ሰራተኞች እና የምዕራብ አርሲ ዞን ነዋሪዎች ለመከላከያ ድጋፍ አደረጉ

55

መቱ/ሻሸመኔ ሕዳር 16/2014 (ኢዜአ): በኢሉባቦር ዞን የመንግስት ሰራተኞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሲያደርጉ የምዕራብ አርሲ ዞንም ለ3ኛ ዙር 211 ሰንጋ በሬዎችን ለመከላከያ ድጋፍ አድርገዋል።

በኢሉባቦር ዞን የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርገዋል።

የወር ደመወዛቸውን ድጋፍ ያደረጉት ሰራተኞቹ እንዳሉት በአሸባሪው ህወሓት ተደቀነው ወቅታዊ የሕልውና አደጋ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ በአጠረ ጊዜ እንዲቀለበስ ድጋፋችን ቀጣይ ነው።

ከሰራተኞቹ መካከል ወይዘሮ ትዕግሥት አስጨናቂ የሀገርን ሉዓላዊነትን ለማስከበር የሕይወት መስዕዋትነት ጭምር እየከፈለ ላለው ሠራዊት ያደረጉት ድጋፍ በጣም ትንሹን መሆኑን ተናግረዋል።

ሕይወቱን እየሰጠ ላለው  ሠራዊት ያደረጉት ድጋፍ እየከፈለ ካለው መስዕዋትነት ጋር የማይነፃፀር ነው  ያሉት ደግሞ ሌላው ሰራተኛ አቶ ጣሰዉ አሰፋ ናቸው።  

ከሀገር ሕልውና የሚቀድምና የሚሰሰሰት ነገር ከቶውንም ስለማይኖር ድጋፋቸውን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ፅጌ ረጋሳም የሀገር ሕልውናና ሉዓላዊነት ፈተናው እስኪታለፍ ድረስ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለ ደምሴ እንዳሉት የዞኑ የመንግሥት ሰራተኞች እስካሁን  ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

በተመሳሳይ የምዕራብ አርሲ ዞን ነዋሪዎች ለሕልውና ዘመቻው ስኬት ለሦስተኛ ጊዜ 211 ስንጋ በሬዎችን ለመከላከያ ስራዊት ድጋፍ አድርገዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሃጅ  ድጋፉን በተመለከተ እንደተናገሩት የዞኑ ሕዝብ አሸባሪው ህውሓት ጦርነት ከከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ለሕልውና ዘመቻው ስኬት ያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

ዞኑ ለሦስተኛ ጊዜ ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 211 ሰንጋ በሬዎችን ማበርከቱን ለአብነት ያነሱት አቶ አህመድ፣ ሴቶችም ስንቅ በማዘጋጀት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው እንዳሉት ዞኑ እስካሁን በጥሬ ገንዘብ 116 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ ወጣቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ኢትዮጵያን ለማዳን ወደ ግንባር መዝመት በከፍተኛ መነሳሳት ውስጥ ናቸው።