ሕክምናዬን ትቼ ሠልፉን የተሳተፍኩት ታሞ ለመታከም ነጻነቷ የተጠበቀች አገር ስለምታስፈልግ ነው

70

ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) አባት አርበኞችና በርካታ የከተማዋ ወጣቶች በቀን ፋኖስ በማብራት በአዲስ አበባ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ኤምባሲዎች በራፎች ላይ የተቃውሞ ሠልፍ አካሂደዋል።

በሠልፉ ከታደሙት ወጣቶች መካከል ዮዲት ደምሴ በሕክምና ቦታ እንደነበረች ገልጻለች።

ይሁንና ምዕራባዊያን እያሳደሩት ያለው ተጽዕኖ ኢትዮጵያዊያንን አገር አልባ የማድረግና አንድነታችንን የማዳከም ተግባር በመሆኑ፤ አገር ስትነካ እያመመኝ ቢሆንም ድርጊቱን ለመቃወም መጥቻለሁ ብላለች።

ሌላዋ የሠላማዊ ሠልፉ ተሳታፊ ሩሃማ ፍቃደእግዚብሄር ለመጀመሪያ ጊዜ ለሠልፍ መወጣቷን ተናግራለች።

ለተቃውሞ ሠልፍ የመውጣቷ ምክንያትም በኢኮኖሚ ያደጉት ምዕራባዊያን በሌሎች አገራት የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ኢ-ፍትሃዊ በመሆኑ ለማውገዝ እንደሆነ ነው የገለጸችው።

ሠላማዊ ሠልፈኞቹ ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን በተመለከተ እየነዙት ያለው ሐሰተኛ መረጃና ሉዓላዊት አገር ላይ የሚያደረጉትን ጣልቃ ገብነት ማቆም አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሌሎች አገራት ሃያላን መጥተው ሲወሩትና የውክልና ጦርነት ሲከፍቱበት ነጻነቱን አሳልፎ የሚሰጥ አለመሆኑን ሊረዱ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና እንደ አህጉርም ዘመናዊ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ውጤት በመሆኑ አፍሪካዊያንም ይህን በመመከት በኩል ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው እንዲደግፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሠላማዊ ሠልፈኞቹ በአዲስ አበባ የሩሲያ እና የኬንያ ኤምባሲዎች በኩል ሲያልፉም ከኢትዮጵያ ጋር ላላቸው መልካም አጋርነት የምስጋና ድምጻቸውን አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም