የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ተግባራዊ በመደረጉ ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል

61

ህዳር 16/2014 (ኢዜአ) የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ተግባራዊ በመደረጉ ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በተጨማሪ 30 ቀናት የሚፈጀውን የደንበኞች አገልግሎት ወደ 2 ቀናት ዝቅ ማድረግ መቻሉንም ነው የገለጸው፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አተገባበር ሂደት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ፤ ተቋሙ ለአንድ ዓመት ከግማሽ የአንድ መስኮት ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ተግባራዊ አድርጓል ብለዋል።

አገልግሎቱ የንግዱ ዘርፍ ለመቆጣጠርና ለመከታተል አመች መሆኑንና በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋለውን የኢኮኖሚ አሻጥር መከላከል መቻሉን ጠቁመዋል።

በገቢዎች ሚኒስቴር የአንድ መስኮት ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ጽህፈት ቤት የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ተስፋዬ አገልግሎቱ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ 73 ተቋማትና 20 ሺህ ነጋዴዎችን በማስተሳሰር ተጠቃሚ ማድርግ መቻሉንም እንዲሁ።

በአገልግሎት ሰጭ ተቋማትና በነጋዴዎች በአካል የነበረውን የተንዛዛና ረጀም ጊዜ ሲውስድ ነበረውን አሰራር በማሳጠር ከ30 ቀናት ወደ 2 ቀን ዝቅ ማድርግ መቻሉን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ የወረቀትና ትራንስፖርት ወጪን የቀነሰ አሰራር መሆኑን ገልጸው በዚህም 70 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን እንደተቻለም ነው ያስረዱት።

አገልግሎት አሰጣጥ የገቢና ወጭ ንግድን በማሳለጥና ኢንቨስትምንትን በመሳብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለውም ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ መረጃዎችን በጥንቃቄ ለማስቀመጥ እንደሚያስችል ተናግረው በዚህም ተቋማትና የንግዱ ማኅበረሰብ መረጃቸውን ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽነት ይበልጥ ለማስፋት የኔትወርክ ዝርጋታና  የሳይበር  ደኅንንት ፕሮጀክት  ማስፋፊያ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።