የጸጥታ ኃይሉ የባቲና ከሚሴ ግንባር በወሰደው የተቀናጀ እርምጃ የጠላትን ጦር ሲመሩ የነበሩ 12 አመራሮች ተደመሰሱ

69

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጸጥታ ኃይሉ የባቲና ከሚሴ ግንባር በወሰደው የተቀናጀ እርምጃ የጠላትን ጦር ሲመሩ የነበሩ 12 አመራሮች መደምሰሳቸውን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በስጡት መግለጫ የተደመሰሱት የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ኃይል አመራሮች በሀገር ክህደት ወንጀል የሚፈለጉ ናቸው፡፡

በአንፃሩ ጠላት ሕዝብን በከፍተኛ ደረጃ ወደ ጦርነቱ በመማገድ ሕዝብን ጨራሽ ስትራቴጂን ተከትሏል። ባለፉት 2 ቀናት በባቲ ግንባር በተደረገ ልዩ ኦፕሬሽን 6 የአርሚ እና የኮር ከፍተኛ መራሮች ተደምስሰዋል።

እነዚህም በፌደራል መንግሥት በሀገር ክህደት ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ ከሐዲ ጀኔራሎችና ኮሎኔሎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚሁ በባቲ ግንባር በዛሬው ዕለት በተደረገው ከፍተኛ የማጥቃት እርምጃ ቀደም ሲል ከነበሩ ጥቃቶች ተርፎ ለዳግም ማጥቃት ሲዘጋጅ የነበረው ጠላት የተደመሰሰ ሲሆን፤ እግሬ አውጪኝ ብሎ ወደ ኋላ የፈረጠጠውን ጠላት የወገን ጦር እያጸዳ ወደ ፊት እየገሰገሰ ነው።

በተጨማሪም በከሚሴ ግንባር በተለያየ ቦታ በተደረገ ልዩ ኦፕሬሽን የግንባሩን የጠላት ጦር ሲመሩ የነበሩ 6 ከሐዲ ከፍተኛ የጦር አመራሮች ከነጠባቂዎቻቸው ተደምስሰዋል።

በሌሎችም ግንባሮች ጠላት በከፍተኛ ሁኔታ እየተመታ ሲሆን፣ የወገንን ክንድ መቋቋም አቅቶት በተናጠልና በቡድን ወደ ኋላ የሚሸሸው ሃይል ዘረፋ እንዳይፈጽምና ንብረት እንዳያወድም በመከላከል ኅብረተሰቡ ተደራጅቶ አካባቢውን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም