የተከፈተብንን የህልውና ጦርነት ለመመከት ተዘጋጅተናል- የአርባምንጭ ነዋሪዎች

አርባ ምንጭ ህዳር 15/2014 ዓ/ም /ኢዜአ/ በውስጥና በውጭ ሀይሎች የተከፈተብንን ሀገር የማፍረስ የህልውና ጦርነት ለመመከት ግንባር ከመዝመት ጀምሮ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ በመቀበል ለመዝመት መዘጋጀታቸውን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት የሆነን  ዘካሪያስ እንደገለጸችው አሁን ላይ ኢትዮጵያ ተገዳ እያካሄደች ያለችው ጦርነት ከአንድ አሸባሪ ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን በእጅ አዙር ቅኝ ሊገዟት ከሚፈልጉ የውጭ ሀይሎች ጋር ጭምር ነው።

"ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች አፍሪካዊት አገር እንደመሆኗ ዛሬ መልኩን ቀይሮ ለመጣው ዘመናዊ  የባሪያ ስርአት አትንበረከክም"  ብላለች ።

"እየተካሄደብን ያለውን የህልውና ጦርነት ለመመከት አቅም በፈቀደ ሁሉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን " ስትል ገልጻለች ።

ከተማው ነዋሪና የጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ታመነ ተስፋዬ በበኩላቸው "ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ሲዘርፍና ሲጨቁን የነበረው አሸባሪው ህወሃት ህዝብን ከጠላት ሲከላከል የነበረውን ሠራዊት ከጀርባው ሆኖ ከመጨፍጨፉ በላይ የእናቴን ልጅ ጨምሮ በሲኖትራክ በመደፍጠጥ በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ታሪክ ፈጽሟል" ብለዋል ፡፡

ቡድኑ ከዚህ ቀደም የፈጸመው ግፍ ሳይበቃው አሁን ላይ የኢትዮጵያን እድገትና ነጻነት እንዲሁም አሁን ላይ የመጣውን ለውጥ ከማይፈልጉ የውጭ ሀይሎችን አላማ ለማሳካት በሀገርና ህዝብ ላይ ጦርነት መክፈቱን ተናግረዋል ።

"እኛ ሁሌም ለማኝ ሆነን እንድንኖር እንዲሁም የመስራትና የማሰብ ባህላችን እንዳያድግ ተኝተው የማያድሩ ምዕራባዊያን ዛሬ ከአሸባሪው ቡድን ጎን ሆነው ቢዋጉንም እኛ የጀግንነት እንጂ የሽንፈት ታሪክ የለንም" ብለዋል፡፡

"አባቶቻችን በዱር በገደሉ መስዋእነት ከፍለው ያስረከቡንን አገር ክብሯን ጠብቀን ለትውልድ የማስረከብ ግዴታ አለብን " ያሉት አቶ ታመነ ኢትዮጵያዊያን ሀገር ለማረስ የተሰነሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች የከፈቱትን ጦርነት ለመመከት በአንድነት ልንቆም ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሀገርን ህልውና ለመታደግ ካላቸው ጽኑ አቋም  ግንባር መዝመታቸው መነሳሳት የፈጠረባቸው መሆኑን ጠቁመው ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ጎን በመሰለፍ የሚፈለገውን መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል የስራ ባልደረቦቻቸውን በማስተባበር ለመዝመት መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።

"ሳንወድ የገባንበት ጦርነት ከአሸባሪዎች ብቻ ሳይሆን ከሴረኞቹ ምዕራባዊያን ጋር ጭምር በመሆኑ ከተባበርን የመጨረሻውን ድል እንጎናጸፋለን" ስሉም አመልክተዋል፡፡

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገር ለማዳን የወሰኑት ውሳኔ ምን ያህል አገር ወዳድ እንደሆኑና እኛም ምን ያህል ለአገራችን መስዋዕት መክፈል እንዳለብን ያመላከተ ነው "ያለው ደግሞ  ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት ንዋይ በላይነህ ናቸው፡፡

"አጼ ሚኒልክና ቴዎድሮስ አገር ለማዳን በጦር ሜዳ መዋደቃቸውን ያወኩት ከታሪክ ቢሆንም ዶክተር አብይ ይህን ታሪክ በዘመኔ ሲደግሙ ማየቴ አኩርቶኛል" ብሏል፡፡

የሀገርን ህልውና ለመታደግ ግንባር እስከ መዝመት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም